የባንኩ ሠራተኞች 127ኛውን የአድዋ ድል በዓል አከበሩ - National Bank

የባንኩ ሠራተኞች 127ኛውን የአድዋ ድል በዓል አከበሩ

የባንኩ ሠራተኞች 127ኛውን የአድዋ ድል በዓል አከበሩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት 127ኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት አከበሩ።

የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በባንኩ አዳራሽ በተከናወነው ሥነሥርዓት ላይ የማኔጅመንት አባላትና የባንኩ ሠራተኞች፣ የተገኙ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ሁነቶች መርሐግብሩ ተከናውኗል።

መርሐግብሩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኮርፖሬት ሰርቪስ ም/ገዥ አቶ እዮብ ገብረኢየሱስ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ብሎም ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።

የአድዋ ድል ጥቁር ሕዝብም አሸናፊ እንደሆነ ለነጮቹም ሆነ ለመላው ዓለም ትምህርት የሠጠ መሆኑንና ለጸረ-ኮሎኒያሊዝም ትግል መነሻ ሊሆን እንደቻለ ታላላቅ ምሁራንና የአገራት መሪዎች ያረጋገጡት ጉዳይ መሆኑንንም አቶ እዮብ  አብነት ጠቅሰው አስረድተዋል።

ም/ገዢው እንዳስረዱት ከኔልሰን ማንዴላ ቀጥሎ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት ታቦ ምቤኪ በአንድ ወቅት ባደረጉት ገለጻ የአድዋ ድል ለነጮች የሚያስደነግጥ ትምህርት የሠጠ፤ ለተቀረው የዓለም ሕዝብ የነፃነት ፋና ወጊ መሆን የቻለ ትልቅ የታሪክ ክስተት መሆኑን አስረድተዋል።

“በመሆኑም የዘንድሮውን 127ኛ የአድዋ ድል በዓል ስናከብር አባቶቻችን ምን ያህል አኩሪ ታሪክ ሠርተው ያለፉ መሆኑን የምናስታውስበትና እኛም በአንድነት፣ በጀግንነትና በጽናት ታሪክ መሥራት የሚጠበቅብን መሆኑን ያስረዳል” ሲሉ አቶ እዮብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የለውጥ ማኔጅመንት፣ ዕቅድና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አባተ ምትኩ አድዋን በተመለከተ ባቀረቡት አጭር ገለጻ፣ አድዋ በአባቶቻችን ከፍተኛ ተጋድልዎ የተደረገበትና በሚያስደንቅ ጀግንነት ድል የተገኘበት ጦርነት መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ አባተ በገለጻቸው ስለ ጠርነቱ መንስዔ፣ ስለጣሊያኖች ዝግጅት፣ በአፄ ምኒልክ ስለተደረገው ጥሪ፣  እቴጌ ጣይቱ ለጣሊያን መንግሥት ስላስተላለፉት መልዕክት፣ ስለሃይል አሰላለፍ በመጨረሻም ስለተካሄደው ጦርነትና አባቶቻችን ስለተጎናጸፉት ድል አብራርተዋል።

በመርሐግብሩ በኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር አማካኝነት ኪናዊ ዝግጅት የቀረበ ሲሆን፣ የዳቦ ቆረሳ፣ ቡና የማፍላት ሥነሥርዓት መካሄዱ ለዝግጅቱ ድምቀት ሆኗል።

በመርሐግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ አድዋን በተመለከተ የጥያቄና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ም/ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀውን ሥጦታ ሸልመዋል።

ም/ገዢው አቶ ፍቃዱ ድጋፌ በመጨረሻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ጊዜ በአገር ላይ የሚመጡ የውጭ ጥቃቶችን ለመቀልበስ በአንድነት የሚነሱ መሆናቸውን የአድዋ ድል ትክክለኛ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል። በመሆኑም በአድዋ ጦርነት ወቅት በአባቶቻችን ዘንድ የታየውን አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት አሁን ደግሞ እኛ ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ላይ መረባረብ እንዳለብን ምክትል ገዥው አሳስበዋል።

The National Bank of Ethiopia was established in 1963 by proclamation 206 of 1963 and began operation in January 1964.

P.O.Box: 5550
Tel: +251 115 517 430
E-mail: nbeinfo@nbe.gov.et
Fax: +251 115 514 588
Avenue: Sudan Street

Navigation

Follow Us