የባንኩ ሴት ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን አከበሩ - National Bank

የባንኩ ሴት ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን አከበሩ

የባንኩ ሴት ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን አከበሩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሴት ሠራተኞች የዘንድሮውን የዓለም የሴቶች ቀን በድምቀት አከበሩ። ቀኑ “እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል በአገርአቀፍ ደረጃ ለ47ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል።

የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በባንኩ አዳራሽ የተከናወነውን ሥነሥርዓት በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኮርፖሬት ሰርቪስ ም/ገዥ አቶ እዮብ ገብረኢየሱስ ዕለቱ ተከብሮ የሚውለው ለሴቶች የማይመቹ ሁኔታዎችን ማስወገድና በተለያየ መልክ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መታገል እንደሚገባ ለማስገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል።

በርግጥም “እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚለው መሪ መልዕክት መሠረት ሁላችንም ጭቆናና ጥቃቶችን ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል።

በተቋም ደረጃ ለሴቶች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ አቅማቸውን ማሳደግና ወደ ሥልጣን ማምጣት የባንኩ አመራር የሚረዳው ጉዳይ ነው ያሉት ም/ገዢው፣ ሴቶችም በበኩላቸው ለዚህ አስተዋፅኦ ማድረግና ዝግጁ ሆኖ መገኘት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

የባንኩ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቺፍ ኦፊሰር የሆኑት ወይዘሮ አምባወርቅ መኮንን ዕለቱን አስመልክቶ በሠጡት ገለጻ የሴቶችን ጉዳይ በሁለንተናዊ መልኩ ለመድረስ የማያቋርጥ ትግል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ዕለቱ በአገራችን ለ47ኛ፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ112ኛ ጊዜ ቢከበርም፣ አሁንም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አልቀረም፤ ሴቶችን ማጎናጸፍ የሚገባው ድል ገና በሚገባ ማሳካት አልተቻለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕለቱን አስመልክቶ ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ ያደካሄዳቸውን መርሐግብሮች ያስታወሱት ወይዘሮ አምባወርቅ፣ በተጓዳኝም የባንኩን ሴት ሠራተኞች ከቁጥር፣ ከትምህርት ዝግጅትና አመራር ላይ ካላቸው ተሳትፎ አኳያ በአሀዝ በተደገፈ መረጃ ማብራሪያ ሠጥተዋል።

በመርሐግብሩ መሠረት ከባንኮች ክሊኒክ የመጡ ዶክተሮች በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር ላይ ትምህርታዊ ገለጻ የሠጡ ሲሆን፣ ከኦፕሪፍስ መጠለያ ማዕከል በመጡ ሕጻናት ኪናዊ ዝግጅት ቀርቧል፤ የዳቦ ቆረሳና ቡና የማፍላት ሥነሥርዓትም ተካሂዷል።

የኦፕሪፍስ ማዕከል ሀላፊ ወይዘሮ እንግዳወርቅ ታደሰ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀደም ሲል በህዳር 2015 ዓ.ም በማዕከሉ ተገኝቶ ያደረገውን ጉብኝትና ድጋፍ አስታውሰው፣ በቀጣይም ባንኩ ለማዕከሉ የሚያደርገው ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሁሉም ወላጅ ልጆቹን (ሴቶችንም ሆነ ወንድ ልጆቹን) በቤትም ሆነ በውጭ፣ እንዲሁም ከቅርብ ዘመድም ጭምር መጠበቅ እንዳለበት ማዕከሉ የሚንከባከባቸው የጥቃት ሰለባ ሕጻናት መልክዕት መሆኑን ወይዘሮ እንግዳወርቅ አሳስበዋል። ምክንያቱም አብዛኞቹ ጥቃቶች ከሩቅ ሳይሆን ከቅርብ በተለይም “የእኔ” ከሚሉት ወገን የሚመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመጨረሻም የለውጥ ማኔጅመንት፣ ዕቅድና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አባተ ምትኩ እንዳሉት፣ “እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ” የሚለውን መሪ ቃል ሁሉም ከልቡ ተግባራዊ ማድረግ አለበት።

በተቋም ደረጃ ሴት ሠራተኞችን በአቅም ግንባታ ከማሳደግና ወደ አመራር ሠጪነት እንዲበቁ ከማድረግ ጎን ለጎን ባንኩን ለሴቶች አመቺ የሥራ ቦታ እንዲሆንላቸው ሁሉንም አስቻይ ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የሕጻናት ማቆያ (day care) ማዕከሉን ግንባታና ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቅቆ በፍጥነት ሥራ ላይ ማዋል የሚያስፈልግ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አባተ፣ ይህም የባንኩ ሴት ሠራተኞች ሥራቸውን በተረጋጋና በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ለማስቻል በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ነፍሰጡር እናቶች በመንግሥት የተሠጣቸው የወሊድ ፈቃድ አጠቃቀም ላይ በራሳቸው በነፍሰጡሮቹ ፍላጎት መሠረት ተመቻችቶ ተግባራዊ ቢደረግ መልካም መሆኑን አቶ አባተ ጠቁመዋል።

በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው በሴት የሴቶች ቀን ላይ የባንኩ መካከለኛና ከፍተኛ ሴት አመራር አባላት እንደሚጠበቀው አለመሳተፋቸውን እንደክፍተት አንስተውታል።           አቶ አባተ በየዓመቱ መጠነኛም ቢሆን ለተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እየሠጠንና ደማቅ በሆነ ሁኔታ እንድናከብር ለሚፈቅድልን የባንኩን የበላይ አመራር፣ እንዲሁም ጥሪያችንን አክብረው በበዓሉ ላይ ለሚታደሙ ሠራተኞች፣ በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር ላይ ትምህርታዊ ገለጻ ለሰጡት ዶክተሮች በመጨረሻም ለኦፕሪፍስ ማዕከል ምሥጋና አቅርበዋል።

The National Bank of Ethiopia was established in 1963 by proclamation 206 of 1963 and began operation in January 1964.

P.O.Box: 5550
Tel: +251 115 517 430
E-mail: nbeinfo@nbe.gov.et
Fax: +251 115 514 588
Avenue: Sudan Street

Navigation

Follow Us