የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ሥራ ሊጀምር ነው
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድን (Deposit Insurance) ሥራ ለማስጀመር የሚስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ባጸደቀው ደንብ ቁጥር 482/2013 መሠረት መቋቋሙን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፈንዱን በበላይነት የሚመሩ አምስት የቦርድ አባላትን ሾመዋል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በሰብሳቢነት የተሾሙ ሲሆን፣ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ መርጋ ዋቅወያ፣ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጃ ዘበነ፣ እንዲሁም የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ከበደ የቦርዱ አባል ሆነው እንዲሰሩ የተመደቡ መሆናቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተላከው ደብዳቤ አመልክቷል።
የቦርዱ አባል አቶ ፍሬዘር አያሌው ለዜና ኢብባ እንደገለጹት፣ ፈንዱን ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ፖሊሲ ፕሮሲጀርና መዋቅር የማዘጋጀት፣ ሃላፊ የመመደብና ሠራተኞች የማሟላት እንዲሁም የፈንድ ካፒታል የማሰባሰብና ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈንዱ ራሱን ችሎ እስኪደራጅ ድረስ የቢሮ ዕቃዎችን የማሟላትና ሠራተኛ የመቅጠር ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አቶ ፍሬዘር ጠቁመዋል።
የፈንዱ አባላት ከሕብረተሰቡ ተቀማጭ ገንዘብ የሚሰበስቡ የፋይናንስ ተቋማት (ባንኮችና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት) መሆናቸውን አቶ ፍሬዘር አመልክተዋል።
የፈንዱ ገንዘብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ሂሳብ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን፣ ሁሉም አባል የፋይናንስ ተቋማት በፈንዱ የሚወሰነውን መነሻ የዓረቦን ክፍያ ወደ ፈንዱ ሂሳብ ገቢ ያደርጋሉ። መንግሥትም መነሻ ካፒታል እንዲሆን ለፈንዱ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር እንደሚመድብ ደንቡ ደንግጓል።
ፈንዱ የተለያዩ የሀብት መሰብሰቢያ መንገዶችን መጠቀም እንደሚችል በደንቡ ውስጥ የተደነገገ ሲሆን፣ የዓረቦን ክፍያዎችን ከአባል የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ መዋጮዎችን እንደመንግሥትና የልማት አጋሮች ካሉ ሌሎች ምንጮች መሰብሰብና ወደ ራሱ ገቢ ማድረግ እንደሚችል ሥልጣን ተሠጥቶታል።
ፈንዱ ከወደቁ ወይም ከፈረሱ የፋይናንስ ተቋማት ንብረት ማጣራት ከሚገኝ ተመላሽ ገንዘብና በቦርዱ ከሚፀድቁ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮች ከሚገኝ ገንዘብ ተጠቃሚ ይሆናል። የፈንዱን ሀብት ገቢ በሚያስገኙለት ዘርፎች ኢንቨስት የማድረግና የማስተዳደር መብት እንዳለውም ተደንግጓል።
ፈንዱን ማቋቋም ያስፈለገው በኢትዮጵያ ቀጣይ የኢኮኖሚ እዴገት የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት ጤናማ፣ ለአደጋ ያልተጋለጠና የተረጋጋ በማድረግ ለማጠናከርና የገንዘብ አስቀማጮች ጥበቃ ለፋይናንስ ሥርዓት ለማረጋጋት በተጨማሪም የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድን እንደ አንድ ተጨማሪ የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ማረጋጊያ ለማድረግ መሆኑ በደንቡ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ሲሆን፣ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሆኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ ደንግጓል።