-
- ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የተሾሙት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የቦርድ አመራር አባላት ሥራ ጀመሩ።
በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቅ የነበረውን የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን የሚያገለግሉ ስድስት የቦርድ አባላት ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. መሾማቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል።
ሌሎቹ የቦርዱ አባላት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ታዬ፣ ከተመድ የካፒታል ዴቨሎፕመንት ኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ደግሞ (ዶ/ር)ኢዮብ ተስፋዬ ፣የሒሳብና የኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሒክመት አብደላ፣ የሴሬብሩስ ፍሮንቲየርስ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል እና የአዲስ አበባ ዩነቪርሲቲ መምህር አቶ አባተ አበበ ናቸው፡፡
ከኅዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የባለሥልጣኑ የቦርድ አባል ሆነው እንዲሠሩ የተመደቡት እነዚህ የቦርድ አባላት ማክሰኞ ኅዳር 27 ቀን 2015 የመጀመሪያ ስብሰባቸውን አካሂደው ሥራቸውን ጀምረዋል።
እነዚህ ተሿሚዎች በቦርድ አባልነት የተሰየሙት በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1248 /2013 መሠረት ሲሆን፣ በአዋጁ መሠረት የቦርድ አባላቱ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡
በአዋጁ መሠረት የካፒታል ገበያ ማቋቋም ያስፈለገው ካፒታል በማሰባሰብ፣ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዲዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ እና የኢንቨስትመንት ስጋቶችን የመጋራት አሠራርን በማስፋፋት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ እንዲቻል ነው። በተጨማሪም በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ የሚፈጠሩ መዋቅራዊ ስጋቶችን ለመለየት፣ ለመከላከልና ለመቀነስ በካፒታል ገበያ ላይ ጠንካራ የቅርብ ክትትልና የቅኝት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት በማስፈለጉ መሆኑን በአዋጁ ተደንግጓል።