03 ሐምሌ 2015 ዓ.ም | አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን በማዘመን እና አስተማማኝነቱን በመጨመር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል። ይህን ግብ ለማሳካት አንዱ ቁልፍ መሣሪያ መሠረታዊ የዲጂታል መታወቂያ መሆኑ ስለታመነበት፤ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ዙሪያ ያተኮሩ ሁለት መርሀ-ግብሮችን መጀመራችንን በደስታ እየገለፅን፤ እነዚህ መርሀ-ግብሮች የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማዘመን እና የሃገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማጎልበት ለሚደረገው ጉዞ በር ከፋች እንደሚሆን ይታመናል።
የመጀመሪያው መርሃ-ግብር ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን በ2016 በጀት ዓመት ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት በማስገባት የተሻለ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የዚህ መርሃ-ግብር ዓላማ ለሀገሪቱ ነዋሪዎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማስፋፋት ሲሆን ፤ ይህም ሂደት የተመዝጋቢውን ግላዊ መረጃዎች ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት እና የመረጃ ደህንነትን በማረጋገጥ የሚከናወን ይሆናል። ይህ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ የተሰጡትም ሆነ ፤ ከዚህ በሗላ በዚህ ስርዓት የሚሰጡ የዲጂታል መታወቂያዎች፤ በሃገሪቱ በሚገኙ የትኛውም የፋይናንስ ተቋማትም ሆነ ዲጂታል ስርዓቶች ተቀባይነት ይኖራቸዋል።
ሁለተኛው መርሀ-ግብር የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ እና የፋይናንስ ስርዓት ደህንነትን ለማስጠበቅ በማቀድ በዘርፉ በኤሌክትሮኒክ ደንበኛህን እወቅ (eKYC) ሂደት ውስጥ የዲጂታል መታወቂያን መጠቀም ነው። ይህ አካሄድ የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚን ትክክለኛ ማንነት በማረጋገጥ የፋይናንስ ግብይቶች ደህንነትን ለመጠበቅ እና ተያያዥ ስጋቶችን በእጅጉ ለመቀነስ ከማስቻሉም ባሻገር አንድን የአገሪቱ ነዋሪ በአካል መምጣት ሳያስፈልግ በዲጂታል አማራጭ ብቻ ደንበኛ ለማድረግ ያስችላል። በዚህም ይህ የብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ፤ የገንዘብ መጭበርበርን በመቀነስ ፥ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በመጨመር እና የተሻሻለ የደንበኞችን የማንነት ማረጋገጫ ስርዓት በመዘርጋት የተጠናከረ የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት ያስችላል።
የዲጂታል መታወቂያ በፋይናንስ ዘርፍ መተግበር በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ግልጽነትን እና አካታችነትን በማጎልበት ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ የጋራ መርሀ-ግብር ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የዲጂታል ፋይናንስ ስነ-ምህዳር ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል።