የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ዘርፍ የቁጥጥር እና የክትትል ማዕቀፍን ለማጠናከር የሚያስችሉ የህግ ማሻሻያዎች ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በህግ በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የፋይናንስ ዘርፉን ደህንነት እና መረጋጋት ለማስጠበቅ በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረት የባንክ ስራን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አምስት መመሪያዎችን አሻሽሏል። መመሪያዎቹን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በሥራ ላይ ያለውን የባንክ ዘርፍ የቁጥጥር ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መርሆዎች (Basel Core Principles for Banking Supervision) እና ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲሁም የባንክ ዘርፍ ከደረሰበት ዕድገት ጋር የተጣጣመ በማድረግ ዘርፉ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡


በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት አምስት የተሻሻሉ መመሪያዎችን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡


እነዚህም መመሪያዎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች መመደብ ይቻላል። በመጀመሪያው ምድብ የሚካተቱት “የብድር ተጋላጭነት ጣሪያ ስለመወሰን”፤ “ከባንኩ ጋር ዝምድና/ግንኙነት ባላቸው ወገኖች አማካኝነት ስለሚኖር የብድር ተጋላጭነት” እንዲሁም “ስለንብረት ምደባ እና ለተዛማጅ ስጋቶች ስለሚያዝ የመጠባበቂያ ፕሮቪዥን” በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ናቸው። ዓላማቸውም የባንኮችን የአደጋ ተጋላጭነት መቀነስ እና የስጋት አስተዳደር ማዕቀፋቸውን በማጠናከር የበለጠ ጤናማ እና አስተማማኝ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።


በሁለተኛው ምድብ የሚካተቱት መመሪያዎች በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አካላት ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ መስፈርቶች እና የኩባንያ አስተዳደርን የሚመለከቱ ናቸው። የእነዚህ መመሪያዎች ዐላማ በባንኮች ውስጥ ያለው የኩባንያ አመራር ሥርዓት ዓለም ከደረሰበት ውጤታማ የኩባንያ አመራር እና አስተዳደር መርሆዎች እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ የባንኮችን ውጤታማነት ማረጋገጥ ነው፡፡

በመመሪያዎቹ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች፡

  1. ከፍተኛ የብድር ተጋላጭነት ገደብ መመሪያ፡ የዚህ መመሪያ ዓላማ አንድ ተበዳሪ (ተያያዥነት ያላቸው ወገኖችን ጨምሮ) ከባንኩ ጋር በገባው ውል መሠረት ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ ምክንያት በባንኩ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ለመቀነስ እና የባንኮች የተጋላጭነት መጠንን በወቅቱ ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂ ፖሊሲ እና አሠራር እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው። መመሪያው በባዝል መርህ መሠረት ማንኛውም ባንክ ለአንድ ወይም ተያያዥነት ላላቸው ደንበኞች የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከሀያ አምስት በመቶ (25%) እንዳይበልጥ ገድቧል፡፡ ይህ መመሪያ ተያያዥነት ያላቸው አካላት እንደ አንድ የባንክ ተበዳሪ ሆነው እንዲቆጠሩ ይደነግጋል።
  2. ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት የሚሰጥ የብድር ተጋላጭነት ገደብ መመሪያ፡ የዚህ መመሪያ ዓላማ አንድ ባንክ ተዛማጅነት ካላቸው አካላት ጋር በሚያደርገው ግንኑነት ብድር አግባብነት በሌለው መንገድ እንዳይሰጥ፣ የጥቅም ግጭት ለመቀነስ እንዲሁም ተዛማጅነት ካላቸው አካላት ጋር ባንኮች የሚያደርጉትን ማንኛውም ግብይት በተመለከተ በቂ ክትትል ለማድረግ እና ያለ አድልዎ በተገቢው መንገድ የተሰጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።

ይህ መመሪያ በዋነኛነት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ገደቦች ጥሏል፡

ሀ) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንኩ ጠቅላላ ከፒታል ከ15% እንዳይበልጥ፤
ለ) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በሙሉ በማንኛውም ጊዜ የሚኖር አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንክ ጠቅላላ ካፒታል ከ35% እንዳይበልጥ፤
ሐ) አንድ ባንክ ተዛማጅ ከሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ከማናቸውም ተዛማጅ ካልሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ተግባራዊ በሚደረግ ሁኔታዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ እንዲሆን እና ከዚህ በተለየ ሁኔታ እንዳይፈጸም ይደነግጋል።

  1. የንብረት ምደባ እና ለተዛማጅ ስጋቶች ስለሚያዝ የመጠባበቂያ ፕሮቪዥን መመሪያ፡ የዚህ መመሪያ ዓላማ የባንኮችን የአደጋ ስጋት አስተዳደር ለማረጋገጥ ሲባል ብድሮች ወይም ቅድመ ክፍያዎች ተቀባይነት ካላቸው የዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ መርሆዎች እና የቁጥጥር ደረጃዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ በየጊዜው እንዲገመገሙ እና በተገቢው መደብ እንዲመደቡ ማድረግ ነው።

ይህ መመሪያ በዋነኛነት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ገደቦች ጥሏል፡

ሀ) ከባንኩ ካፒታል ከአምስት በመቶ (5%) በላይ የሆኑትን እና የውል ማሻሻያ የተደረገባቸውን ብድሮች አጠቃላይ መረጃ በየጊዜው ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንዲደረግ ያስገድዳል።
ለ) በባዝል መርህ መሠረት አንድ ወቅቱን ጠብቆ መከፈል ያልቻለ እና ለተበላሸ ብድር የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላ ብድር ለብድሩ መያዣነት የቀረበው ዋስትና ምንም ይሁን ምን እንደ ተበላሸ ብድር ተወስዶ ወለድ የማይከፈልበት ምድብ ውስጥ መካተት ይኖርበታል፡፡
ሐ) አንድ ተበዳሪ ከአንድ ባንክ የተለያዩ ብድሮችን የወሰደ ከሆነ እና ከብድሮቹ አንዱ የተበላሸ ከሆነ ይህ የተበላሸው ብድር ባንኩ ለደንበኛው ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ወይም ተጋላጭነት 20% እና ከዛ በላይ ከሆነ ሁሉም ብድሮች ወዲያውኑ በተበላሸ ብድር መደብ ውስጥ ይካተታሉ።

መ) አንድ ብድር ምንም እንኳን የመክፈያ ጊዜው ያልደረሰ ቢሆንም በተለያዩ ክስተቶች እና ሁኔታዎች ሳቢያ ብድሩን በቀጣይ ለመክፈል የሚያስችል እድል የጠበበ እና የተመናመነ እንደሆነ አመላካች ሁኔታ ካለ ብድሩ እንደ ተበላሸ ብድር ተቆጥሮ ቢያንስ “አጠራጣሪ ብድሮች” የሚል መደብ ላይ መካተት ይኖርበታል፡፡

ሠ) ብድርን ሁልጊዜ ጤናማ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከል ለባንክ በሚፈቀደው ከፍተኛ የብድር ውል የማሻሻል ድግግሞሽ መጠን ላይ ገደብ ጥሏል። በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ ብድሮች አምስት ጊዜ ይፈቀድ የነበረውን የማሻሻል ድግግሞሽ ከሦስት ጊዜ እንዳይበልጥ፤ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ብድር እስከ ስድስት ጊዜ ይፈቀድ የነበረው ድግግሞሽ ከአራት ጊዜ እንዳይበልጥ ደንግጓል፡፡

  1. በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ላላቸው ሰዎች የሚውሉ መስፈርቶች መመሪያ: የዚህ መመሪያ ዓላማ የባንክ ዘርፍን መረጋጋት እና የረጅም ጊዜ ተቋማዊ ስኬት ለማረጋገጥ፣ ብቁ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለቤቶች፣ ዳይሬክተሮች እና ሥራ አስፈፃሚዎች እንዲኖሩት በማድረግ የባንኮች አጠቃላይ አስተዳደር ውጤታማነት በማስቀጠል በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ አመኔታን ለማስጠበቅ ነው።
  2. የኩባንያ አስተዳደር መመሪያ፡ የዚህ መመሪያ ዓላማ ጠንካራ የኩባንያ አስተዳደር እንዲኖር ማስቻል ሲሆን ይህም የአክሲዮን ባለቤቶችን እሴት፣ የደንበኞችን እና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን የረጅም ጊዜ ፍላጎቶች ለማሟላት፣ ተጋላጭነትን እና ተመጣጣኝ ስጋትን የማስተናገድ አቅምን፣ የንግድ ጠንቃቃነትን፣ ተቋማዊ ተጠያቂነትን ለማሳደግ ነው። ማሻሻያው ገለልተኛ የሆኑ ግለሰቦች በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት የሚካተቱበትን አስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ በቦርድ ምርጫ ሂደት፣ በቦርድ ሹመት እና በአስመራጭ ኮሚቴዎች ተግባራት ላይ ለውጦች አድርጓል፤ አካታችነት እና ልዩነትን ለማስተናገድ ይቻል ዘንድ መመሪያው ቢያንስ ሁለት ሴቶች በቦርድ አባልነት የሚካተቱበትን አሰገዳጅ ድንጋጌ አካቷል፡፡

በመጨረሻም እነዚህን የወጡ መመሪያዎች ባንኮች በጥብቅ እንዲተገብሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በዚህ አጋጣሚ ያሳስባል፡፡

More News