መስከረም 22 ቀን 2017 ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር አሁን በሥራ ላይ ካሉት ከባንክ ጋር ከተያያዙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ከባንክ ጋር ዝምድና የሌላቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ መመሪያ (NBE Foreign Exchange Directive No. FXD/01/2024) ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረት፣ ከዚህ የሚከተሉት አምስት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ በመመሪያው ንኡስ አንቀጽ 4.2 መሠረት እንዲንቀሳቀሱ የሥራ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡
- Dugda Fidelity Investment PLC
- Ethio Independent Foreign Exchange Bureau
- Global Independent Foreign Exchange Bureau
- Robust Independent Foreign Exchange Bureau
- Yoga Forex Bureau
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለማስፋፋትና ለማዳበር የሚረዳ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዥ ወዲያውኑ የሚፈጸም (spot transaction) ብቻ ይሆናል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት ይችላሉ፡፡ አንዲሁም ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ ይችላሉ፡፡
በመጨረሻም፣ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ የአሠራር፣ የደህንነት፣ የሪፖርት አደራረግና የመዝገብ አያያዝ መስፈርቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ባንኩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ያስታውቃል፡፡