የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ማስታወቂያ

የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ያካሄዳል። ለጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፣ ጨረታው ለሁሉም ባንኮች ክፍት ይሆናል፡፡

ሐምሌ 2016 የተጀመረውን አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ረፎርም ፕሮግራም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በተለይም፣ የወጪ ንግድ፣ ሐዋላና የካፒታል ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል አሳይተዋል፡፡ በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ወርቅን ወደ ውጭ የመላክ ብቸኛ ሥልጣን ላለው ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የባንኩ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት እጅግ አበራታች ሆኗል፡፡

የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት መጨመር የሪፎርሙ ጥሩና አዎንታዊ ውጤት ቢሆንም፣ የማዕከላዊ ባንኩን ጥብቅ የገንዘብ ዕድገት ፖሊሲና የዋጋ ንረት ግብ ስኬት በማያደናቅፍ መልኩ ሊተገበር ይገባል፡፡ በመሆኑም ከባንኩ የወርቅ ግዥ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ለማለዘብና በማዕከላዊ ባንኩ እጅ ካለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከፊሉን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት በገበያው ላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሻሻል ባንኩ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች በጨረታ ለመሸጥ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሁኔታን በቅርበት በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ሽያጮችን የሚያካሂድ ሲሆን፣ ይህም የባንኩን የዋጋና የውጭ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን ያስቀመጠው ስትራቴጂአዊ ግብ አካል ነው፡፡

      በመሆኑም፣ ባንኮች ከዚህ በታች በተመለከተው አኳኌንና የጊዜ ማዕቀፍ በጨረታው እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል፡-

ጨረታው የሚካሄድበት ቀን፡ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017
የጨረታው ሰነድ የሚቀርበብት ሜይል፡fxauction@nbe.gov.et
የጨረታው ሰነድ የሚቀርብበት ጊዜ፡ከጠዋቱ 4 እስከ 6 ሰዓት
የጨረታው ውጤት የሚገለጽበት ሰዓት፡ከቀኑ 9 ሰዓት
ሂሳቡ የሚወራረድበት የመጨረሻ ቀን፡የካቲት 18 ቀን 2017

More Archive