የውጭ ምንዛሪ ገበያ ማሻሻያዎች

ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓትን በይበልጥ ለማሻሻል ከዛሬ ጀምሮ የተወሰኑ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ እነዚህ የለውጥ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ከዓለም አቀፍ አሠራር ጋር ከማጣጣም ባሻገር ለአስመጪዎችና ለውጭ ሀገር ተጓዦች የተሻለ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ እንዲሁም፣ በአሁኑ ወቅት ለባንክ ሥርዓት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለመፍጠር የሚረዱ በየሁለት ሳምንት የሚደረጉ ጨረታዎችን የመሳሰሉ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቶችን የሚያሻሽሉ ጅምሮችን የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡

ካለፈው ሐምሌ ወር 2016 ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት በውጭ ምንዛሪ ገበያ እንዲሁም በሀገሪቱ የውጭ ክፍያ ሚዛን ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማምጣቱ ይታወሳል፡፡  በውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ረገድ የተደረጉ ማሻሻያዎች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ከማሳደግ ባሻገር የሸቀጦች ወጪ ንግድ በእጥፍ እንዲጨምር፣የአገልግሎትና የሐዋላ ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግና የግልም ሆነ የመንግሥት የካፒታል ፍሰት እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ የንግድ ባንኮችና የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መሻሻል ነጋዴዎችና አምራቾች ወሳኝ የሆኑ ግብአቶችን እንዲያገኙ፣ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ሥራዎቻቸውን እንዲያስፋፉ አስችሏቸዋል፡፡

ዛሬ የተደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎች፣ እስካሁን የተገኙ አዎንታዊ ውጤቶችን ከማጠናከር ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓትን በይበልጥ ለማጠናከር የሚረዱ ናቸው፡፡ ዐበይት ለውጦቹም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

  1. ለአስመጪዎች የቅድመ ክፍያ (አድቫንስ ፐይመንት) መጠንን ከፍ ማድረግ፡- ይህ የማሻሻያ እርምጃ አስመጪዎች ለውጭ ሀገራት አቅራቢዎቻቸው የሚያደርጉትን የውጭ ምንዛሪ ቅድመ ክፍያ (አድቫንስ ፐይመንት) መጠን የሚገድበውን የቆየ አሠራር ለመለወጥ ይረዳል፡፡ በመሆኑም፣ ብሔራዊ ባንክ በአስመጪዎች ላይ የተጣለውን የቅድመ ክፍያ ገደብ ከፍ አድርጓል፡፡ ከአቻ ሀገራት ተሞክሮ በመነሣትና ለብዙ ዓመታት ለውጥ ሳይደረግበት የቆየውን አሠራር የመለወጥን አስፈላጊነት በመገንዘብ፣ ሸቀጦችን ከውጭ ለማስገባት ሊከፈል የሚችለውን የቅድመ ክፍያ መጠን ከ5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወደ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር  ከፍ ተደርጓል፡፡
  2.  ለውጭ ሀገር ተጓዦች የሚፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን ከፍ ማድረግ፡- ለውጭ ሀገር ተጓዦች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ወደ ውጭ ሀገር ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን በጥሬ ገንዘብ የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ መጠን እንዲጨምር  ተደርጓል፡፡ በአዲሱ ገደብ መሠረት ለግል ተጓዦች የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ወደ 10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ለንግድ ሥራ መንገደኞች ደግሞ 15 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሆኗል፡፡ ይህንንም የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ወይም በካርድ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ግለሰቦች ከሂሳባቸው ላይ በካርድ መጠቀም የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከ10 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡
  3. የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክፍያዎችን ሥርዓት ማስያዝ፡-  በኢትዮጵያ የሚሠራባቸውን ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ አስተዳደራዊ ክፍያዎችን ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ሲባል ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የሚያስከፍሏቸው ወጪዎች ተወዳዳሪነትን፣ ግልጸኝነትንና ምቹነትን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያበረታታል፡፡ በዚሁ መሠረት፣ ከገቢ ንግድ፣ ከአገልግሎት ክፍያ ወይም ከጥሬ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የሚያስከፍሏቸው ማናቸውም አስተዳደራዊ ወጪዎችና ክፍያዎች ከግንቦት 18፣ 2017 ጀምሮ ከ4 በመቶ እንዳይበልጡ ተወስኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ጋር የተያያዙ አስተዳደራዊ ወጪዎች ለተጠቃሚዎች ግልጽና ቀላል መሆናቸውን ለማረጋገጥ  ሲባል ባንኮች የሚያስከፍሏቸውን የተለያዩ ተጨማሪና ጥቃቅን የአገልግሎት ወጪዎች እንዲያስቀሩ ባንኩ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ በመጨረሻም፣ ከውጭ ምንዛሪ ግብይት ጋር የተያያዙ የባንኮችን አስተዳደራዊ ክፍያዎች ግልጽነት ለማረጋገጥ ብሔራዊ ባንክ ከሰኔ ወር 2017 ጀምሮ በድረ ገጹ ላይ መረጃዎቹን በመደበኛነት ለሕዝቡ ይፋ ያደርጋል፡፡

ከላይ የተገለጹት ከውጭ ምንዛሪ ገበያ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ማሻሻያዎች ቀልጣፋ፣ ተወዳዳሪና ጥልቀት ያለው እንዲሁም የሀገሪቱን የፋይናንስ ደንበኞችና የግሉን ዘርፍ መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚያሟላ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለመፍጠር እንደሚረዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጽኑ ያምናል፡፡

More News