የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት የችግኝ ተከላ (አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ) መርሐ ግብር አካሄዱ።
መርሐ ግብሩ ሐሙስ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም አቃቂ በሚገኘው የፋይናንስ ጥናት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር ማሞ ምህረቱ መርሐግብሩን ሲያስጀምሩ፣ በየዓመቱ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ ቀደም ሲል የተተከሉትም ለውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዕለቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 700 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ “የዚህ ታሪካዊ ቀን ተካፋይ በመሆናችን ሁላችንንም እንኳን ደስ ያለን” በማለት ችግኝ ተከላውን አስጀምረዋል።
በመርሐ ግብሩ አገር በቀል የሆኑና ለግቢው አረንጓዴ ውበትን የሚያላብሱ፣ ነፋሻማ አየርን የሚያድሉ እንዲሁም ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች ተተክለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባጠቃላይ አቃቂ/ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የአትዮጵያ የፋይናንስ ጥናት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ከ22ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል፣ እንዲሁም ችግኝ ገዝቶ በማስረከብና አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን ለወዳጅነት ፓርክ በማበርከት የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱ ይታወሳል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው በዚህ መርሐግብር አጠቃላይ 40 ቢሊዮን በላይ ችግኖች በመትከል የኢትዮጵያን የደን ሽፋን 23.6% ማድረስ ተችሏል።
በተያዘው ዓመትም 7.5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እና የሀገሪቱን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ዘመቻው እየተካሄደ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።






