የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች “ብሔራዊ ጥቅምና የጂኦስትራቴጂ ቁመና” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ በወቅታዊ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄዱ።
አርብ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጻ አድርገዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በገለጻቸው ስለ ብሔራዊ ጥቅምና ኢትዮጵያ ስላላት የጂኦስትራቴጂ ቁመና፣ ምንነት፣ ዕሳቤዎቹ፣ ፋይዳዎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔያቸው እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋና ተቋም የሚጠበቅበትን ሚና በዝርዝር አስረድተዋል።
ብሔራዊ ጥቅም አምስት ቁልፍ ግቦች እንዳሉት የጠቀሱት ሚኒስት ዴኤታው፣ እነርሱም አገራዊ ህልውናና ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና፣ ፖለቲካዊ አቅምና ተጽዕኖ፣ የባህል ነጻነትና የሕዝቦች ማህበራዊ ልማት መሆናቸውን አስረድተዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ ከትናንት በተወረሰና ነገን በሚወስን ቁልፍ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በባዳ መሪነት እንዲሁም በባንዳ አስተባባሪነትና መሣሪያነት ዳግም ጦርነት ለመክፈት ዛሬም ጠላቶቻችን እየተንደረደሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የታሪካዊ ጠላቶቻችን ያልተገራ ዘመን ተሻጋሪ ፍላጎት፣ የባንዳዎች በየዘመኑ ለታሪካዊ ጠላቶች መከራየት፣ የኢትዮጵያ ጂኦስትራቴጂያዊ ተፈላጊነት የፈጠረው ስጋት፣ የአገረ መንግሥት ግንባታ አለመጠናቀቅ፣ ድህነትና ሁዋላ ቀርነት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች የብሔራዊ ጥቅማችን ዋነኛ ፈተናዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
እነዚህ ፈተናዎች የአገራችንን ደህንነትና ሰላም እንደተፈታተኑ፣ አገራችንን በድህነት ውስጥ እንዳቆዩዋት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን እንዳሰናከለው፣ የሕዝባችንን ማህበራዊ ልማትና ፍትሕ እንዳስተጓጎለው፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የሚገባትን ቁመና እንዳትይዝ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው መፍትሔ ያሏቸውን ሐሳቦች የጠቆሙ ሲሆን፣ በታደሰ ቁመና አዲሱን ዓለም መዋጀት፣ ውስጣዊ አንድነት ላይ መሥራት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን ማጠንከር፣ የጠላትን የውጊያ አቅም መስበር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥና የዲፕሎማሲ አቅምን መገንባት መሆናቸውን አስረድተዋል።
በመሆኑም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትር ደኤታው፣ የመንግሥት ተቋማት በሁለንተናዊ መልኩ የሚጠበቅባቸውን መወጣት፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖን ማጎልበት እንደሚገባቸው ሁሉ ዜጎችም በችግሮች አለመታሰርና በርዕይ መጠንከር እንደሚገባቸው አብራርተዋል።
ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከባህር በር ጥያቄና ወደብ ከማግኘት ጋር የታያዙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የባህር በር ጥያቄና ወደብ የማግኘት ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው፤ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቅርብ ነው። በሚገባ ይረዳዋል። የተወሰደብንን መብት ለማስመለስ አሁን መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው፤ ነገር ግን የዘገየ ነው፤ ኤክስፖርትና ኢምፖርትን ለማቀላጠፍ ወደብ የማግኘት ጉዳይ አያጠያይቅም፤ ከሶማሌላንድ ጋር በወደብ ጉዳይ ላይ የተካሄደ ስምምነት ነበር፤ ከምን ደረሰ? የኢትዮጵያን ማንሠራራት ጠላቶቻችን አይፈልጉምና መፍትሔው ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ፣ የውስጥ አቅማችንን ማጎልበትና ከሁሉም በላይ ሰላማችንን ማረጋገጥና አንድነታችንን ማጠናከር ነው፤ የሚሉት ይገኙባቸዋል።
በተጨማሪም የወደብ ጉዳይን ልናሳካ የምንችልባቸው መንገዶች እንዴት ያሉ ናቸው? በውድም ሆነ በግድ፤ በሰላም ካልተቻለ በማንኛውም መንገድ የሚለው ስሜት መር አገላለጽ ትክክለኛ ነውን? ጦርነትን ለማስተናገድ ጊዜው አሁን ነውን? ሉዓላዊነትን አስከብሮ ለመቆየት ነባራዊ ሁኔታን ከግንዛቤ ማስገባት ይኖርብናል። በወኔ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ብቃት ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ዘመኑን መዋጀት ይገባል። የሳይበር ምህዳሩ ላይ ኢትዮጵያ ያላት ዝግጁነት እንዴት ይታያል? የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።
በመጨረሻም ለጥያቄዎቹና አስተያየቶቹ ሚኒስትር ዴኤታው ምላሽና ማብራሪያ ሠጥተዋል። ጦርነት እንደአማራጭ የሚታሰብ አለመሆኑን፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም መንግሥት በሚገባ የሚገነዘበው መሆኑንም አብራርተዋል።















