ከቶሮንቶ ማዕከል ጋር በመተባበር የሥልጠና መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቶሮንቶ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር በማክሮ እና በማይክሮ ፕሩዴንሻል ቁጥጥር ዘዴዎች ላይ ያዘጋጀው የአንድ ሳምንት ሥልጠና ተካሄደ።


ሥልጠናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የቶሮንቶ የሥልጠና ማዕከል መካከል ከዚህ ቀደም የደረሱበትን ስምምነት መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ሥልጠናውም ከግንቦት 05 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ግንቦት 09 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተካሄዷል፡፡


ተሳታፊዎች ፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያለውን ስጋትና አደጋ ለመገምገም እና የማክሮፕሩዴንሻል (Macro prudential) ፖሊሲ ምክሮችን ለማዘጋጀትና የማክሮፕሩዴንሻል (Macro prudential) ጠቋሚዎችን የመመርመር አቅምን ለማሻሻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡


በሥልጠናው ማስጀመርያ መድረክ ላይ ተገኘተው የመከፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ፤ ከቶሮንቶ ሥልጠና ማዕከል የሚገኝ ትምህርት የብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር አቅምን ለማሻሻልና የባንክ ቁጥጥር ዘዴን ለማዘመን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ክቡር ገዥ አክለውም የብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች ከፍተኛ ልምድ ካለው የቶሮንቶ ሥልጠና ማዕከል የሚያገኙት የቴክኒክ እውቀት የባንኩን ቁጥጥር ሥርዓት ለመቀየር እና የፋይናንስ ተቋማት የበለጠ አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።


ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ ባንክ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ይህ ዓይነት ስልጠናና ቀጣይነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ወሳኝ መሆኑን ክቡር ገዥው አብራርተዋል።


በሥልጠናው ወቅት ከቴክኖሎጅ መዘመን ጋር ተያይዘው የሚመጡ አዳኢስ ስጋቶችን፣ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የሚመጣ ስጋት (cyber risk) እና የአየር ንብረት ለውጥ በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚያደርሰው ስጋት ታሳቢ ያደረገ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡


የማይክሮ ፕሩዴንሻል ቁጥጥር (Micro prudential supervision) ዘዴ፤ (የአንድ ፋይናንስ ተቋም ደህንነትና ጤናማነት እንዲሁም የባለሀብቶች/ኢንቨስተሮች ጥበቃ ላይ የሚያተኮር የቁጥጥር ሥርዓት) እና የማክሮ ፕሩዴንሻል (Macro prudential supervision) ዘዴ፤ በአጠቃላይ የገንዘብ ሥርዓቱ ጤናማነትና መረጋጋት ላይ የሚያጠነጥን የቁጥጥር ሥርዓት አጣምሮ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተበራርቷል፡፡

More News