የክልል ፋይናንስ አካታችነት ትግበራ ማዕቀፍ ላይ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክልል ፋይናንስ አካታችነት ትግበራ ማዕቀፍ ነድፎ ከጋምቤላ፣ ከሶማሌ እና ከኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤቶች እና ግብረ ኃይል አባላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ፡


የምክክር መድረኩ የተካሄደው በብሔራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ-ሁለት ላይ ተመስርቶ በተዘጋጀው የክልል ፋይናንስ አካታችነት ትግበራ ማዕቀፍ ላይ ሲሆን የማዕቀፉ ዋና ዓላማ በክልሎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ ነው።


እንዲሁም በመጀመሪያው ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ-አንድ ትግበራ ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለመሙላትና እና በክልሎች መካከል እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች መካከል የሚስተዋለውን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነት ልዩነት ለማጠበብ የታለመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡


የምክክር ፎረሙ ለሁሉም የክልል ፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤቶች እና የግብረ ሃይል አባላት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በቀጣይነት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ አማካሪ ወይዘሮ ማርታ ኃይለማርያም በመክፈቻ ንግግራቸው የብሔራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ-ሁለት 2021-2025፤ በመጀመሪያው ፋይናንስ አካታችነት ትግበራ ወቅት የተስተዋሉ ክፍተቶችን ከመሙላት ባሻገር የሀገሪቱን ፋይናንስ አካታችነት ደረጃ እ.አ.አ በ2025 ድረስ ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡


እንደ ወ/ሮ ማርታ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ-ሁለት 11 ዋና ዋና ፕሮግራሞች እና በርካታ የድርጊት መርኃ ግብሮች ያሉት ሲሆን፣ በዋነኛነት የዲጂታል ፋይናንስ፣ የሴቶች የፋይናንስ ተጠቃሚነትና የሸሪዓ ሥርዓት የፋይናንስ አገልግሎትና ምርቶች ተደራሽነትን ለማስፋፋት ግብ አስቀምጧል፡፡


በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፋይናንስ አካታችነት ደረጃ 46 በመቶ ሲሆን ይህም ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። ኬንያ 83 በመቶ፣ ሩዋንዳ 77 በመቶ እና ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት አማካይ 55 በመቶ ሽፋን እንዳላቸው ወ/ሮ ማሪታ ገልጸዋል፡፡


በክልሎች መካከል ያለው ፋይናንስ አካታችነት ልዩነት ከ6 በመቶ እስከ 75 በመቶ ያህል የሠፋ ነው። በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው ፋይናንስ አካታችነት ደግሞ 19 በመቶ ያህል ልዩነት ያለው ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ፋይናንስ አካታችነት ደረጃ 75 በመቶ፣ የጋምቤላ ክልል 35፣ የኦሮሚያ ክልል 27 በመቶ ሲሆን የሶማሌ ክልል ፋይናንስ አካታችነት ደረጃ 6 በመቶ ነው ብቻ ነው፡፡


በምክክር ፎረሙ ላይ የክልል ፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤቶች እና ግብረ ኃይል አባላት የፋይናንስ ተደራሽነትን የማሳደግ እና ለክልሎች ተስማሚ የሆኑ የፋይናንስ ምርቶችና አገልግሎቶችን የማስፋፋት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡


በተጨማሪም የክልል ፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤቶች እና ግብረ ኃይል አባላት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የክልል ፋይናንስ አካታችነት ማዕቀፍን የመምራት እና የመተግበር ኃላፊነት ተሰጥተቸዋል፡፡


በተጨማሪም የፋይናንስ አካታችነት ደረጃ ለማሻሻል፣ የብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂ 2021-2025 (NFES)፣ ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ 2021-2024 (NDPS) እና ተንቀሳቃሽ የንብረት ደህንነት መብት በትክክል መተግበር እንዳለባት አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡


በምክክሩ ወቅት የክልል ፋይናንስ አካታችነት ማዕቀፍ፣ የብሔራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ-II 2021-2025፣ ብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂ 2021-2025 እና ተንቀሳቃሽ የንብረት ደህንነት መብት ላይ ጽሁፎች ቀርበዋል። በተሳታፊዎቹ የተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ላይ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

More News