የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ አደረገ

ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዋናነት ዝቀተኛና የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህም ከባንኩ የመካከለኛ ዘመን ስትራቴጂአዊ ዕቅዶች መካከል ቀዳሚው ሲሆን፣ ይህንኑ ለማሳካት ባንኩ ሰፊ ሕጋዊ፣ ተቋማዊና ቴክኒካዊ ዝግጅቶችን አድርጓል፡፡ በተለይም የባንኩ ቀዳሚ ዓላማ ዋጋን ማረጋጋት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከዘመናዊ የማዕከላዊ ባንክ አሠራርና ከፈጣን በገበያ ላይ ከተመሠረተ የፋይናንስ ሥርዓት ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን ለመተግበር የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የዝግጅት ሥራዎች በአብዛኛው የተጠናቀቁ በመሆናቸው ብሔራዊ ባንኩ በዛሬው ዕለት አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይፋ አድርጓል፡-

  • አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይሸጋገራል፡፡ በአዲሱ የገንዘብ የፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት ባንኩ በዋናነት የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን ለማሳየትና አጠቃላይ የገንዘብና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ-ነክ የወለድ መጣኔ (National Bank Rate) የሚባለውን የፖሊሲ ተመን (Policy Rate) ይጠቀማል፡፡ ይህ የማዕከላዊ ባንክ የወለድ መጣኔ እንደ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ሁኔታ እየታየ ከፍ ወይም ዝቅ የሚል ይሆናል፡፡
  • ሁለተኛ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንኩ ፖሊሲ-ነክ የወለድ መጣኔ ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ ይሆናል፡፡ ይህ የወለድ መጣኔ ባሁኑ ወቅት የሚታዩ ማክሮ ኢኮኖሚአዊ ሁኔታዎችን ማለትም፣እየቀነሰ ያለውን፣ነገር ግን አሁንም ከፍ ብሎ የሚታየውን የዋጋ ንረት፣ ዝቅተኛ የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገትና ካለፉት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ የመጣውን የባንክ ብድር ዕድገት ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ-ነክ የወለድ መጣኔ ባሁኑ ጊዜ ባንኮች እርስ በርስ በሚበዳደሩት ብድር ላይ ከሚከፍሉት ወለድ ጋር የተቀራረበ ነገር ግን ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጧቸው ብድሮች ላይ ከሚያስከፍሉት ከ16-20 በመቶ ከሚደርስ ወለድ ያነሰ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፣ይህ የብሔራዊ ባንክ የወለድ መጣኔ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ ተመን የሚመለከት አለመሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ባንኮች በውድድር ላይ ተመሥርተው ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን በራሳቸው መወሰናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እንዲሁም ባሁኑ ጊዜ ባንኮች በቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ዝቅተኛው የ7 በመቶ ወለድ በዚህ በብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን ምክንያት ለውጥ አይደረግበትም፡
  • ሶስተኛ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ጨረታዎችን በየሁለት ሳምንቱ ያካሂዳል፡፡ እነዚህ ጨረታዎች የሚደረጉት ብሔራዊ ባንኩ ከወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሣት ከባንክ ሥርዓቱ ውስጥ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ እንዲያስችለው ነው፡፡ እነዚህ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ጋር የሚያደርጋቸው ጨረታዎች በዋናነት የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የፖሊሲ-ነክ የወለድ መጣኔ እምብዛም የተራራቀ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያላግባብ የተከማቸ የገንዘብ መጠን መኖር የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ ተመኑን ከማዕከላዊ ባንኩ ፖሊሲ- ነክ የወለድ መጣኔ በእጅጉ እንዲቀንስ የሚያደርግ ከሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ሥርዓቱ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከባንኮች ጋር የሚገበያይበትን ጨረታ ያካሂዳል፡፡ በአንጻሩ ፣ በአጠቃላይ የባንክ ሥርዓት ውስጥ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥምና የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የፖሊሲ ተመን ከፍ ያለ እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ተጨማሪ ገንዘብ ለማቅረብ ይህንኑ ጨረታ ይጠቀማል፡፡
  • አራተኛ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የአንድ ቀን የብድር አገልግሎት (overnight lending facility) እና የአንድ ቀን የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (overnight deposit facility) ይሰጣል፡፡ እነዚህ የአንድ ቀን የብድር ወይም የተቀማጭ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ምክንያት ባንኮች የአጭር ጊዜ የገንዘብ ፍሰት አቋማቸውን ለማስተካከል እንዲረዳቸው ነው፡፡ እነዚህ ቋሚ አገልግሎቶች የሚሰጡት ከብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን 3 በመቶ በማስበለጥ ወይም በማሳነስ ይሆናል፡፡
  • አምስተኛ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች እርስ በርስ የሚበዳደሩበትን የተነቃቃ የገንዘብ ገበያ ለመመሥረት የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት በቅርቡ ለመዘርጋት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የገንዘብ ገበያው በኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት ላይ ተመሥርቶ በሚገባ ሥራ ላይ ሲውል ትርፍ ገንዘብ ያላቸው ባንኮች የገንዘብ እጥረት ላጋጠማቸው ባንኮች ማበደር ይችላሉ፡፡ በመሆኑም፣ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ወይም ትርፍ ገንዘብ ሲኖራቸው እርስ በርስ የመገበያየት ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ አሠራር ሥራ ላይ ሲውል የባንክ ለባንክ የወለድ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የፖሊሲ-ነከ የወለድ መጣኔ ጋር የሚጣጣም ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ግን ብሔራዊ ባንኩ ሁኔታውን ለማስተካከል ከባንኮች ጋር የግብይት ጨረታን ይጠቀማል፡፡
  • ስድስተኛ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ቢሸጋገርም፣ በሽግግሩ ወቅት ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቀጥታ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች በጊዜያዊነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማስተላለፊያ ዘዴዎች ከተጠበቀው በላይ ዝግ ያሉ ከሆኑ፣ ብሔራዊ ባንክ ነባሮቹን ቀጥተኛ የፖሊሲ መሣሪያዎች በተጨማሪነት ይጠቀምባቸዋል፡፡ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደፊት አቅጣጫ ይሰጥበታል፡፡

ማጠቃለያ


ዛሬ ይፋ የተደረገው ለውጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘመንና አሠራሩን ከዓለም ማዕከላዊ ባንኮች መልካም ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣም ረገድ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ እርምጃ ነው፡፡ የባንኩን ፖሊሲ- ነክ የወለድ መጣኔ መወሰን፣ ከባንኮች ጋር የግብይት ጨረታ መጀመር፣ የአንድ ቀን የብድርና የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግና የባንክ ለባንክ የገበያ ሥርዓት ማዘጋጀት ብሔራዊ ባንኩ በስትራቴጂአዊ ዕቅዱና በባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በአግባቡ ለመወጣት እጅግ አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፣ በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረጉ ለውጦች በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፍ የሚታዩ አንዳንድ ሥር የሰደዱ ድክመቶችን ለማስወገድ እንደሚረዱ ብሔራዊ ባንኩ በጽኑ ያምናል፡፡ ስለሆነም፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዚህ ለአዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ያልተቆጠበ ትብብራቸውን እንዲለግሱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

More News