ማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2023 ዓ.ም በባንኩ አዳራሽ በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ ስምምነቱን የተፈራረሙት አቶ ሰሎሞን ደስታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ እና ሚስ ማዳሎ ሚናፉ የዓለምአቀፉ የፋይናንስ ተቋም (አይኤፍሲ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው።
ሥምምነቱ የብድር መሠረተልማትን በማጠናከር፣ ተደራሽ ላልሆኑ አካላት የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋፋት (Strengthening Credit Infrastructure – Promoting Access to Finance for the Unserved/Underserved) የሚል ዓላማ ያለው ነው።
በሥምምነቱ መሠረት የዓለምአቀፉ የፋይናንስ ተቋም (አይኤፍሲ) ይህ ዓላማ በኢትዮጵያ እንዲሳካ ለማስቻል ለባንኩ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።
ከቴክኒክ ድጋፎቹ የብሔራዊ ባንክ የክሬዲት ሬፈረንስ ሥራ እንዲዘምን የማድረግ፣ የሥራ ክፍሉን አደረጃጀት ማሳደግና አቅም ግንባታ የማካሄድ፣ ብድርን የተመለከቱ መረጃዎች ላይ አዳዲስ አመዘጋገብን ወይም አማራጭ የመረጃ አያያዝን የማጎልበት፣ እንደ መረጃ አስተዳደርና ትንተና ያሉ አዳዲስ አገልግሎቶች ሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ የመሥጠት ያሉት ይገኙባቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የብድር መሠረተልማትን በማጠናከር ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለማቅረብ፣ የብድር ስጋቶችን መቀነስና ለመቆጣጠር እንዲሁም ለግሉ ክፍለኢኮኖሚ ብድር በሠፊው የሚቀርብበትን አግባብ ለማስፋት የሚያስችለውን አቅም ለማሳደግ ያስችለዋል።
የዓለምአቀፉ የፋይናንስ ተቋም (አይኤፍሲ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ ማዳሎ ሚናፉ የትብብር ሥምምነቱ በትክክል ተግባራዊ ተደርጎ በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ እንደሚመጣ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ አቶ ሰሎሞን ደስታ በበኩላቸው ከዓለምአቀፉ የፋይናንስ ተቋም በተካሄዱ ውይይቶች እዚህ ሥምምነት ላይ መደረስ መቻሉን አድንቀው በተደረሰው ሥምምነት መሠረት ከተቋሙ በሚደረገው የቴክኒክ ድጋፍ የታለመውን ውጤት እንደሚመጣ አረጋግጠዋል።