ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
በአዋጅ ቁጥር 1359/2017 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ምርመራ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የባንክ ደንበኞች በዋናነት የንግድ ድርጅቶችና ግለሰብ ነጋዴዎች ለንግድ ሥራቸው ተብሎ ከተከፈተው እና በሚመለከተው የግብር ሰብሳቢ ተቋም ካስመዘገቡት የባንክ ሒሳቦች ውጭ የግል የባንክ ሂሳባቸው ወይም የሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ ተጠቅመው የተለያዩ የንግድ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እየፈጸሙ መሆናቸውን አረጋግጧል። ይህ አሰራር ከግብር ሰብሳቢ ባለስልጣናት ቁጥጥርና ክትትል ለመሸሽ የሚደረግ ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪ በዚህ አግባብ የሚፈጸሙ የፋይናንስ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች የወንጀል ፍሬ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዙ ወይም የተገናኙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህን መሰል ተግባራትንም ለመግታት አስፈላጊው የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ ተወስኗል።
በመሆኑም የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ታማኝነት እንዲሁም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ደህንነት ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሂሳቦችን ለንግድ እና ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞችን አስመልክቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት እንዲልኩ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

