የባንኩ ሠራተኞች የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አከበሩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት 18ኛውን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከበሩ፡፡

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ!” በሚል መሪ መልዕክት በመላ አገሪቱ ተከብሮ ውሏል።

ሠራተኞቹ በባንኩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባከሄዱት ሥነሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ቺፍ ኢኮኖሚስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ አቶ ፍቃዱ ደግፌ የዘንድሮውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብር ብዙ አገራዊ ስኬቶችን እየዘከርን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአገራዊ ስኬቶች መካከል ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዕውን ማድረጋችን እንዲሁም በሁሉ አቀፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ላይ የተገኙትን እመርታዊ ስኬቶች በአብነት አንስተዋል። በወጪ ንግድ፣ በመንግሥት ገቢ አሰባሰብ፣ በዉጭ ምንዛሪ ክምችት፣ የዋጋ ንረትን በማስተካከልና በመሳሰሉት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል። አያይዘውም ኢኮኖሚያችንን በመሰረቱ የሚቀይሩ አዳዲስ የሜጋ ፕሮጀክቶች መሠረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት መከበሩ የዘንድሮውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን አስተዋጽኦ በተመለከተም ምክትል ገዢው አቶ ፍቃዱ ሲያስረዱ ባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍን ማዘመኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመንና የዋጋ ንረት ማረጋጋቱ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ቁጥጥርን ማጠናከሩና ጤናማ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲኖር ማስቻሉን በአብነት አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሁለት አዋጆችን ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ 1359/2017 እንዲሁም የባንክ ሥራ አዋጅ 1360/2017 አሻሽሎ በሥራ ላይ ማዋሉንና ከሁሉ በላይ ደግሞ የባንክ ሥራን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉ ትልቅ አገራዊ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አቶ ፍቃዱ አብራርተዋል።

ም/ገዥው አያይዘው መላው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኛ እስከ አሁን በተገኙ ድሎች ሳይዘናጋ የሪፎርሙን ስኬታማነት የማረጋጋጥ ሀገራዊ ተልእኮ ለመወጣትና በተያዘው በጀት ዓመትም በአንድነት መንፈስ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የባንኩ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዘርፍ ም/ገዥ አቶ ሰሎሞን ደስታ፣ የኮርፖሬት ሰርቪስ ም/ገዥ አቶ እዮብ ገብረየሱስ እንዲሁም ዳይሬክተሮችና መላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች በሥነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው በዓሉን አክብረዋል።

More News