የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ሪፖርት አጭር መልዕክት
በኢትዮጵያ ጤናማና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ነው። ይህንንም ዓላማ ለማሳካት ከራሱ ከፋይናንስ ዘርፍም ሆነ ከሌሎች የውስጥና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የሚመነጩና የዘርፉን መረጋጋት ሊያውኩ የሚችሉ ስጋቶችን መለየትና መፍትሔ መስጠትን ይጠይቃል።
በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመጀመሪያውን የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ሪፖርት ለሕትመት ሲያበቃ ዋነኛ ዓላማው ለፋይናንስ ዘርፉ ተዋንያን፣ ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት እና ለመላው ሕብረተሰብ የብሔራዊ ባንክን ሙያዊ ትንተናና የፋይናንስ ዘርፉን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን እንዲሁም፣ ከብሔራዊ ባንክ እርምጃዎች በተጨማሪ፣ የፋይናንስ ተቋማት እነዚህን ስጋቶች በመቀነስ ረገድ የሚጫወቱትን የየራሳቸውን ሚና ለማሳወቅ ነው። ሪፖርቱ ሐምሌ 2015 የተካሄደውን የስጋት ተጋላጭነት መመዘኛ መነሻ በማድረግ የፋይናንስ ሥርዓቱን መረጋጋትና የስጋት ተጋላጭነት ደረጃ የሚያሳይ ነው።
የሪፖርቱ ማጠቃለያ ጭብጥ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ሥር የሰደደ ስጋት ባይኖርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ ስጋቶች እየጨመሩ መምጣታቸውንና የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ደህንነት በቀጣይነት ለማረጋገጥ ተገቢ ትኩረት መስጠትና የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ የሚያመለክት ነው፡፡
- በባንክ ዘርፍ የሚታዩ ስጋቶች መለስተኛ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የብድር፣ የጥሬ ገንዘብ አከል ንብረት (ሊኩዊዲቲ)፣ የአሠራር (operational) እና፣ በመጠኑም ቢሆን፣ የገበያ እጥረት ስጋቶች በሪፖርቱ ወቅት ጨምረዋል። ሆኖም፣ ባንኮች በካፒታልና በጥሬ ገንዘብ አከል መጠባበቂያ (በሊኩዊዲቲ ባፈር)፣ እንዲሁም በአስተማማኝ ትርፋማነትና (solid profit) በሌሎች መለኪያዎች ረገድ ጠንካራ ጤናማ እና አስተማማኝ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ባንኮች ስጋቶችን ለመቋቋም እንዲችሉ አቅም ሰጥቷቸዋል። ይህንንም ብሔራዊ ባንኩ ባደረገው የባንኮች አደጋን የመቋቋም ጥንካሬ የሙከራ ጥናት ለማረጋገጥ ተችሏል።
- የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የካፒታል ብቃት መመዘኛ (capital adequacy ratio)፣ የተበላሸ ብድር መመዘኛ (non-performing loan ratio)፣ እና የጥሬ ገንዘብ አከል ሀብት መመዘኛ (liquidity ratio) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጣቸውን መለኪያዎች ያሟሉ ሲሆን፣ በሪፖርቱ ወቅት መሻሻል አሳይተዋል፡፡
- የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ተቋማት ዘርፍም የስጋት ደረጃ መለስተኛ ሲሆን፣ የካፒታል ስጋት፣ የሀብት ጥራት (asset quality) ችግርና ሥር የሰደደ ስጋት ደረጃም ዝቅተኛ ነው፡፡
- የኢንሹራንስ ዘርፉ ችግርን መቋቋም በሚያስችል ጠንካራ መሠረት ላይ ቢሆንም፣ በገቢና በኢንቨስትመንት ክምችት (earnings and concentration) ረገድ ያሉ ስጋቶች ከፍተኛ በመሆናቸው ቁጥጥር ያሻዋል።
- አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ የብድርና የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት ስጋት (credit and deposit concentration risk) ደረጃ ከፍተኛ በመሆኑ ጠበቅ ያለ ቁጥጥርና ክትትል ያስፈልገዋል፡፡
- የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ መሠረተ ልማት በተመለከተ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጉልህ መሻሻል ቢኖርም አሁንም ደካማ በመሆኑ በመዋቅር፣ በአሠራርና በቴክኒክ ብቃት ረገድ ተጨማሪ ማሻሻያ ያስፈልገዋል። በተለይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው የዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ የሚያስከትለውን አደጋ ለመገምገም የዘመነና ግልጽ የሆነ የስጋት መለኪያ የማስቀመጥ ጉዳይ የፖሊሲ ትኩረትና ለተግባራዊነቱ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመሆን የስጋት መቀነሻ ስልቶች መቀየስንና ተጨባጭ ተሳትፎን ከሚጠይቁ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ይህ የፋይናንስ መረጋጋት ሪፖርት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ሪፖርት እንደመሆኑ፣ በዝግጅት ወቅት ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎለታል። በዘርፉ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው አካላት አስተያየቶች ተካትተዋል። በመሆኑም፣ አስቀድሞ ለሕትመት ከተያዘለት በላይ ጊዜ ወስዷል፡፡ በቀጣይ የሚዘጋጁት የፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋት ሪፖርቶች በየዓመቱ ሕዳር ላይ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይታተማሉ። ቀጣዩ ዕትምም እ.አ.አ. በ2024 መጨረሻ ላይ ይፈጸማል።