በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ላይ ያተኮረ አውደጥናት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዳራሽ ተካሄደ።
አርብ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ የኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ታሪክ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን ጥናት አቅርበዋል።
ፕሮፌሰር ሽፈራው በገለጻቸው፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጸጸር ረጅም የሚባል የባንክ አገልግሎት ታሪክ ያላት መሆኗን አመልክተዋል።
አቢሲኒያ ባንክ ተብሎ ከሚታወቀው የመጀሪያው ባንክ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት የተቋቋሙ ባንኮች እንደነበሩ ያመለከቱት ምሁሩ፣ ሆኖም በፋሺስት ጣሊያን ወረራና በሌሎች ተጨማማሪ ምክንያቶች የባንኩ ዘርፍ ብዙ ውጣውረዶችን ለማሳለፍ መገደዱን አስረድተዋል።
በተጠቀሱትና ሌሎች ምክንያቶች የባንኩን ዘርፍ ትክክለኛና ዝርዝር ታሪክ ለማወቅ የሚያስችል በቂ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።
ከዚህ በመነሳት የፋይናንስ ተቋማት ማለትም ባንኮች፣ የመድን ተቋማትና ሌሎችም የፋይናንስ ዘርፍ ተዋናዮች መረጃዎቻቸውን በልዩ ልዩ አግባብ አዘጋጅተውና ሰንደው ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለመላው መረጃ ፈላጊ ሕብረተሰብ ለማቅረብ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ ተቋማቱ አንድም በየራሳቸው፣ አንድም በጋራ ሆነው የመረጃ ባንክ/ማዕከል እንዲያቋቁሙ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ በበኩላቸው በጥናቱ እንደተመለከተው ባንኮችና አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፍ መረጃዎችን የማዘጋጀት፣ ሰንዶ የማስቀመጥና ለሕዝብ ተደራሽ ረግማድ እንደሚገባ አጽንፆት ሠጥተዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች የጀመረ መሆኑን የጠቆሙት ክቡር ገዥው፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የባንክ ታሪክ የያዘ ዶክመንት ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የገንዘብ ሙዚየም የማቋቋም ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።
እንዲሁም የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የሰው ሀይል በሥልጠና ለማብቃት እንዲቻል የተቋቋመውን የኢትዮጵያ የፋይናን ጥናት ተቋምን በሁለንተናዊ መልኩ ለማሳደግና የልዕቀት ማዕከል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ማሞ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ታሪክ እንዲሁም የገንዘብ ፖሊሲ ታሪክ ተጠንቶ በሰነድ መልክ መዘጋጀት እንዳለበት ያመለከቱት አቶ ማሞ፣ ከጣሊያን ወረራ በኋላ በአገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ጉምቱ ሰዎችን እሳቤ፣ እሴታቸውንና ጥረታቸውን የሚዘክር ማስተማሪያ ሰነድ ሊዘጋጅ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ክቡር ገዥው ባንኮችም ሆኑ የመድን ድርጅቶች ብሎም ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አገር አቀፍ የሆነ የመረጃ ማዕከል ለማቋቋም ቀንጅት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ምልዕክት አስተላልፈዋል።
በአውደጥናቱ የባንኮችና የመድን ድርጅቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል።