የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓት መመሪያ ተግባራዊነት መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ

ንግድ ባንኮች በየተቋሞቻቸው የሚታየውን የደንበኞች ቅሬታና የደንበኞች አያያዝ ለማሻሻል የፋይናንስ ጥበቃ ሥርዓት መመሪያ ተግባራዊነት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዘርፍ ም/ገዥ አማካሪ የሆኑት ወ/ሮ ማርታ ሀይለማርያም ከንግድ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ጋር የካቲት 7/2016 ዓ.ም በባንኩ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ ውይይት ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓት ለፋይናንስ ሴክተር ጤናማነት፣ለፋይናንስ አካታችነት ዕድገት እና ለፋይናንስ ሴክተር ደህንነት ያለውን አስተዋጽዖ በመረዳት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አስተውቀዋል፡፡
“በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው የደንበኞች ቅሬታና በአንዳንድ ተቋማት የሚታዩ ተገቢ ያልሆኑ የደንበኞች አያያዝ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል” በማለት አማካሪዋ አስረድተዋል፡፡


የፋይናንስ ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓት ትግበራን ለመምራት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጥበቃና ትምህርት ዳይሬክቶሬት” በቅርቡ ማቋቋሙን ወ/ሮ ማርታ አመልክተዋል፡፡


የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጥበቃና ትምህርት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሙህዲን ሽፋ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እ.አ.አ በኦክቶበር 31,2023 ከባንክ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ሁሉም ባንኮች የፋይናንስ ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓትን እ.አ.አ እስከ ዲሴምበር 31,2023 ድረስ እንዲያቋቁሙ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት መተግበሩን ለማረጋግጥ የመስክ ምርመራ መደረጉን ጠቁመው “በምርመራው ላይ የተገኙትን ክፍተቶች ለሚመለከታችው ባንኮች ክፍተታችውን እንዲያስተካክሉ አሳውቀናል” ብለዋል፡፡


የዕለቱ ውይይት ዓላማም በተገኙ ክፍተቶች ላይና ባንኩ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ መጀመሩን፤ ባንኮቹም በሥራ ላይ በሚገኙ የሕግ ማዕቀፎች መመሪያ መሠረት የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማሳሰብ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ ውይይትም አቶ ሙህዲን በፋይናንስ ተጠቃሚዎች ጥበቃ ሥርዓት ላይ እና በተገኙ ከፍተቶች ላይ አጠር ያለ ገለጻ አቅርበዋል፡፡
በዕለቱ ስብሰባ የተካፈሉት የንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በሸማቾች ጥበቃ መመሪያ ላይ መሻሻል የሚገባቸው ክፍሎች እንዳሉ ጠቁመው፣ እነዚህም ለአተገባበር በሚመች መልኩ መሻሻል እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡


የሸማቾች ጥበቃና መመሪያው “የባንክ ደንበኛ” ብሎ የገለጸው ተበዳሪን እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ነገር ግን በትልቁ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው አስቀማጮች እንደሆኑና ለነሱም ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


አቶ ሙህዲን ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰጡት ምላሽ የሠጡ ሲሆን መመሪያው የተዘጋጀው ዓለምአቀፍ አሠራሮችንና ተሞክሮዎችን መሠረት አድርጎ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


መሻሻል ያለባቸው የመመሪያው ክፍሎች እንደሚሻሻሉ አመልክተው አብዛኛው የመመሪያው ክፍሎች ተግባራዊ ሆነው እንደሚቀጥሉና ለተግባራዊነታቸውም በንግድ ባንኮች በኩል ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡


የደንበኞችን ቅሬታን የመቀበልና የመፍታት ኃላፊነት በዋነኛነት የንግድ ባንኮች መሆኑን ያስረዱት አቶ ሙህዲን በተቀመጠው የቅሬታ አፈታት ሥርዓት መሠረት ኃለፊነትን መወጣት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡


በዚህ ለግማሽ ቀን በተካሄደው ውይይት ከ 30 በላይ የሚሆኑ የንግድ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

More News