፲፰፻፺፯

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በብሪታንያ በቅኝ-ገዥነት ይተዳደር በነበረው የግብፅ ብሔራዊ ባንክ መካከል በተደረገው ሰምምነት መሠረት፤ አቢሲኒያ ባንክ የሚባል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ባንክ ተቋቁሞ የካቲት ፱ ቀን ፲፰፻፺፰ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ሚኒልክ ተመረቆ ተከፈተ::

፲፱፻፳፫

ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የባንክ ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ በሚያሻሽል አግባብ የአቢሲኒያ ባንክን ድርሻ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያዝ በማድረግና ስሙን የኢትዮጵያ ባንክ በማለት በአፍሪካ አህጉር የመጀመሪያውን አገራዊ ባንክ ለመክፈት ችለዋል፡፡ ባነኩም የማዕከላዊ ባንክ እና የንግድ የባንክ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ተደረገ::

፲፱፻፳፰

በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት (፲፱፻፳፰-፲፱፻፴፫) የባንክ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋ ሲሆን በተለይ የጣሊያን ባንኮች እንቅስቃሴ የጎላ ነበር፡፡ ከነፃነት በኋላ በርክሌይ ባንክ በመባል የሚታወቅ የብሪታንያ ባንክ በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ከ ፲፱፻፴፫ እስከ ፲፱፻፴፭ ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የባንክ ሥራ ውስጥ ቆይቷል::

፲፱፻፴፭

በጣሊያን ወረራ ወቅት ፈርሶ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ከነፃነት በኋላ እንደገና የተቋቋመ ሲሆን እንደ ቀድሞው ባንክ የማዕከላዊ ባንክ እና የንግድ የባንክ ሥራዎችን አጣምሮ ይሠራ ነበረ፡፡ በ ፲፱፻፶፭ ሥራውን ባቆመበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ፲፱ የሀገር ውስጥ ቅርንጫፎች፣ በካርቱም አንድ ቅርንጫፎች እና በጅቡቲ የማስተላለፍ ሥራ የሚሠራ ጽ / ቤት ነበረው::

፲፱፻፶፭

የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ እንዲሆን ለሁለት ተከፍሎ አሁን ያለውን ማዕከላዊ የባንክ እና የንግድ የባንክ ሥራዎችን በግልጽ በለየ ሁኔታ እንዲደራጅ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ ፲፱፻፶፭ በአዋጅ ቁጥር ፪፻፮ ተቋቁሞ ሥራውን በ ፲፱፻፶፮ ጀመረ፡፡

፲፱፻፷፯

እንደገና የገንዘብና ባንክ አዋጅ ቁጥር 97/7976 ዓ.ም የብሔራዊ ባንክ ሥራዎች በወቅቱ የነበረው የደርግ የአስተዳደር ሥርዓት ይከተለው በነበረው የሶሻሊስት የኢኮኖሚ መርሆዋችን መሠረት በማድረግ እንዲቀረፅ ተደርገዋል፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ የመድህን ኩበንያዎችን፣ የብድርናና ቁጠባ ተቋማትን እና የኢንቨስትመንት ባንክን እንዲያስተዳድራቸውና እንዲቆጣጠራቸው በአዋጅ ተፈቅደዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ቀድሞ ዶላር በሚል የሚጠራው የኢትዮጵያ ገንዘብ ብር የሚል ሲያሜ እንዲሰጠው ተደርገዋል፡፡

፲፱፻፹፬

የመንግሥት ለውጥ እና በ ፲፱፻፹፬ የተጀመረውን የነፃ ገበያ ፖሊሲን ተከትሎ ብዙ የገንዘብ ተቋማት በዋናነት በገበያ መር የፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ለመሥራት እንደገና ተደራጅተዋል፡፡ የ፲፱፻፹፮ የገንዘብ እና የባንክ አዋጅ ቁጥር ፹፫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት የራሱ የሆኑ ተግባራትና ኃላፊነት ያለው ሆኖ እንዲቋቋም አደረገ፡፡

፲፱፻፴፭

በ አዋጅ ቁጥር ፭፻፺፩ | ፳፻፰ ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጠንካራ የአዋቃቀር ማሻሻያ አደረገ፤ የቁጥጥር ሥራውም ጠነከረ፡፡ አዳዲስ አሠራሮችን ለአብነትም እንደ ሞባይል ባንኪንግ ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲጀመሩና የገንዘብ ተደራሽነትና የፋይናንስ አካታችነት እንዲፋጠን አደረገ፡፡ በርካታ አዳዲስ ባንኮች እና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በመቋቋማቸው የፋይናንስ አገልግሎቶች ተስፋፉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግሥት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት በመፍቀድ የፋይናንስ ዘርፉን ነፃ ለማድረግ ወስኗል፡፡ የውጭ ባንኮች መዕዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱና በባንክ ዘርፍ እንዲገቡ በመፈቀዱ ወደፊቱ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣ ይታመናል፡፡

የቀድሞ ገዥዎች