“ለሴቶች የፋይናንስ ተጠቃሚነትና አመራር ሠጪነት ልዩ ትኩረት ተሠጥቶታል” – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ

በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ሴቶች በአመራር ደረጃ የሚኖራቸውን ሥፍራና ሚና ለማጎልበት እንዲሁም በዘርፉ የሚታየውን የፆታ ተሳትፎ ልዩነት ለማጥበብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትኩረት እንደሚሠራ የባንኩ ገዥ አስታወቁ።

የፋይናንስ ዘርፉን ለሴቶች ተጠቃሚነት በሚል መልዕክት ሐሙስ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ (ኒውፊን) በይፋ ተመሠረቷል።


ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር አቶ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚ ማድረግና ወደ አመራርነት ማሳደግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቅድሚያ የሠጠው ቁልፍ ተግባሩ ነው።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥራ ላይ ባዋለው ሁለተኛው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ (ከ2021 – 25 እ.ኤ.አ) በፋይናንስ ተጠቃሚነት ረገድ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት (ያልተመጣጠነ ተጠቃሚነት) ለማጥበብ ልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውነዋል።


በዚህ የፋይናንስ አካታችነት መርሐግብር አበረታች ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም፣ በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለው የተሳትፎና የተጠቃሚነት ድርሻ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሠፋ መጥቷል። ይህም በፋይናንስ ኢንዱስትሪው እንደ አንድ ትልቅ ክፍተት ሆኖ የሚመዘገብ ነው።


ከዚህ በተጨማሪ በፋይናንስ ተቋማት የሚሠሩ ሴቶች በበቂ ቁጥር ያህል ወደ አመራርነት እንዲመጡ ባለመደረጋቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ሴቶች የዘርፉ ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ለመገንዘብ ተችሏል።


በመሆኑም እስከ 2025 (እ.ኤ.አ) በየተቋማቱ የከፍተኛ ማኔጅመንት አባላት (ማለትም ምክትል ፕሬዚዳንትና ዳይሬክተር ደረጃ ያሉ ኃላፊነቶች) መካከል እስከ 25 በመቶ ያህሉ፤ እንዲሁም ከዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መካከል ቢያንስ አንዷ ሴት መሆን እንዳለባቸው አቶ ማሞ ስትራቴጂውን ጠቅሰው አስረድተዋል።


ዘላቂነትና አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባትም ባንኮችን ጨምሮ በፋይናንስ ዘርፉ የሴቶች ሁለንተናዊ ተካታችነት መረጋገጥ እንደሚገባው አቶ ማሞ ተናግረዋል።


በመሆኑም ለሥርዓተ ፆታ ትልቅ ትኩረት የሚሠጥ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠርና የአገሪቱ ቀዳሚ አጀንዳ የሆነውን የሴቶች የፋይናንስ አካታችነትን ከግብ ለማድረስ የኔትዎርኩ መመሥረት ትልቅ አስቻይ አደረጃጀት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕምነት መሆኑን አስረድተዋል።


በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ተወካይ ዳይሬክተር ዱዩና ፔትረስኩ፤ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉት ትልልቅ ተግባራት ዘርፉን ለማሳደግ አስቻይ መሆናቸውን አመልክተዋል። ከተግባራቱም መካከል የባንኮች ተቀማጭ ፈንድ ማቋቋም እና አካታች የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት ተጠቃሽ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


ሆኖም ሠፊ ክፍተት የሚታይበትን ሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚ የማድረግና በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ለአመራርነት የማብቃት ጉዳይ ትኩረት ሊሠጠው እንደሚገባ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

የኔትወርኩ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መሊካ በድሪ ሲሆኑ፣ እርሳቸው እንዳሉት በፋይናንስ ተቋማት የሴቶች አመራርነት ተሳትፎ ከ12 በመቶ ብቻ ነው።


ወይዘሮ መሊካ የፋይናንስ ተቋማት ለጉዳዩ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልፀው፤ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ሴቶችን በቦርድ አባልነት ያቀፈው ኔትወርኩም ለሁሉ አቀፍ ሴቶች አካታችነት የራሱን ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል። ኮንፈረንሱን በንግግር የዘጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ም/ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ይህንን ወሳኝ ጉዳይ ከግብ ለማድረስ ባንኩ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።


በተመሳሳይ መልኩ የፋይናንስ ተቋማት ሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚ በማድረግና ወደ አመራር ሠጪነት በማሳደግ ረገድ በስትራቴጂው መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።


ሴቶችን ወደ አመራር ደረጃ የሚያሳድግ፣ በሁለንተናዊ መልኩ የሚያበቃና፣ የፆታ እኩልነትን የሚያሰፍን የፋይናንስ ዘርፍ ጎልብቶ ማየት የኒውፊን ራዕዮች ናቸው።

More News