ፈንዱ የግንዛቤ ፈጠራና ውይይት መርሐግብር አካሄደ

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የግንዛቤ ፈጠራና መርሐ ግብር አርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል አካሄደ።


በመርሐግብሩ አቶ ሰለሞን ደስታ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ የቦርድ ሰብሳቢ ባደረጉት ንግግር እንዳስረዱት፣ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ለገንዘብ አስቀማጮች ዋስትና ለመሥጠት ብሎም የፋይናንስ ዘርፉ የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል።


በአሁኑ ወቅት ባንኮችን፣ አንስተኛ የገንዘብ ተቋማትን፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ 117 ያህል የፋይናንስ ተቋማት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ሰሎሞን፣ የተቋማቱ ጠቅላላ ሀብት ከ 3 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር እንዲሁም ተቀማጭ ገንዘብ ደግሞ ከ2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር መብለጡንም አመልክተዋል።


በመሆኑም በተቋማቱ ገንዘብ የሚያስቀምጡ ደንበኞች ለገንዘባቸው ዋስትና ስለሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰዋል። ተቋሙም በዓለም 148ኛው የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ መሆን ችሏል ብለዋል።


ዶ/ር ደሳለኝ አምባው የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው፣ፈንዱ ከተቋቋመበት ከመጋቢት 2015 ዓ.ም ጀምሮ ስላከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ በእስካሁኑ ሂደትም 31 የግል እና የመንግሥት ባንኮች፣ 49 ማይክሮ ፋይንስ ተቋማት አባል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


ከአባል ፋይናንስ ተቋማት ዓረቦን የሚሰብስብ ሲሆን፣ እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም ድረስ ብር 2.8 ቢሊዮን ሰብስቧል፡፡ ከዚህም ከሰበሰበው አረቦን ውስጥ ብር 2.58 ቢሊዮን የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ገዝቷል። ይህም ለፈንዱ ገቢ የሚያስገኝና የፈንዱን የፋይናንስ አቅም የሚያጠናክር መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።፡


በመርሐግብሩ ላይ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ሁሉም የፋይናንስ እንዲሁም ተቀራራቢ የመንግሥት አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው፣ የግንዛቤ ማስፋፋት ሥራን ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራት እንደሚገባ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በሚገባ መጠቀም ብሎም አመቺ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግና ሌሎችም ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል።


በመርሐግብሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከባንኮች፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።


የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 428/2013 የተቋቋመ ሲሆን ለአባል ፋይናንስ ተቋማት (ማለትም ባንኮችና ማይክሮፋይናንስ ተቋማት) አስቀማጮች ጥበቃ በመስጠት ለፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ አባል ፋይናንስ ተቋም ቢወድቅ፣ ፈንዱ ለአንድ ገንዘብ አስቀማጭ እስከ ብር መቶ ሺህ ብር የኢንሹራንስ ሽፋን ይሰጣል፡፡


በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ አሠራር የተዘረጋው እ.ኤ.አ በ1933 በአሜሪካ ነው።

More News