የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት “የምትተክል አገር፤ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት የችግኝ ተከላ (አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ) መርሐ ግብር አካሄዱ።
መርሐ ግብሩ አርብ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም አቃቂ/ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የአትዮጵያ የፋይናንስ ጥናት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥና ዙሪያው ተካሂዷል።
ከአቃቂ/ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 አስተዳደር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በተካሄደው በዚህ መርሐ ግብር ከ4ሺህ የሚበልጡ አገር በቀል የሆኑ የጥላ ዛፍ፣ የፍራፍሬና የአበባ ችግኞች ተተክለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ መርሐ ግብሩን ሲያስጀምሩ እንዳሉት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር አካባቢን ለመጠበቅ፣ አሁን ያለው ትውልድ እንዲጠቀምበት ለማድረግና ለመጪው ትውልድ ተስማሚ አገር ለማቆየት እንዲሁም ሠፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፋይዳ ያለው ነው።
“አረንጓዴ አሻራ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ባህል ለማስረጽ የሚያስችል መርሐ ግብር ነው” ያሉት የባንኩ ገዥ፣ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በተካሄደው አገር አቀፍ ንቅናቄ፣ ችግኝ መትከል የአገራችን መልካም ባህል እየሆነ መምጣቱን መረዳት እንደሚቻል አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባጠቃላይ አቃቂ/ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የአትዮጵያ የፋይናንስ ጥናት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ከ20ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል፣ እንዲሁም ችግኝ ገዝቶ በማስረከብና አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን ለወዳጅነት ፓርክ በማበርከት የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱ ይታወሳል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው በዚህ መርሐግብር አጠቃላይ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከ17.2% ወደ 23.6% ለማድረስ መቻሉን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።