የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ትምህርት ሞጁል ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጣቶች እንዲሁም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በፋይናንስ ዘርፍ ያላቸውን ዕውቀትና ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የፋይናንስ ማስተማሪያ ሰነድ (ሞጁል) ይፋ አደረገ።


የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው የማስተማሪያ ሞጁል ይፋ ማድረጊያ መርሐ-ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ም/ገዥ አማካሪ ወ/ሮ ማርታ ኃይለማርያም እንደተናገሩት፣ ሞጁሉ ብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂን ለማሳካት እንዲቻል የተዘጋጀ ነው።
በመሆኑም በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት፣ በመንግሥትና በልማት አጋር ድርጅቶች በተናጠል እየተከናወኑ ያሉ የፋይናንስ ትምህርት ጥረቶች በተቀናጀ የትብብር መንፈስ መተግበር እንዳለባቸው ወ/ሮ ማርታ አመልክተዋል።


“ይህም እ.ኤ.አ በ2025 የፋይናንስ አገልግሎት ላይ ግንዛቤ ያላቸውን ወጣቶች እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ 75 በመቶ ለማድረስ የምናደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ይታመናል” ሲሉ ገልጸዋል።


የሞጁሉ ዝግጅት በ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ፈርስት ኮንሳልት ብሪጅስ ፕሮግራም ከተባለ ድርጅት ጋር እ.ኤ.አ ከ2022 ጀምሮ በጥምረት ሲካሄድ የነበረ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ማርታ፤ ባጠቃላይ ዝግጅቱ ብሔራዊ ባንክ ያቋቋመው ብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት ግብረ ሀይልን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥትና አጋር የልማት ድርጅቶችን ያሳተፈ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል ያለው፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር በበኩላቸው የመርሐግብሩ በይፋ መጀመር በብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።


ወጣቶችንና ጥቃቅን፤ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማትን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠርና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ በማበርከት ረገድ ወሳኝ ሚና ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል፡፡

አቶ ነቢል ኬሎው፣ የፈርስት ኮንሰልት ማኔጂንግ ዳይሬክተር በበኩላቸው ለወጣቶችና ጥቃቅን፤ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ፋይናንስ ተደራሽነት ዋናው እንቅፋት የሆነው፣ የፋይናንስ እውቀትና ግንዛቤ እጥረት እንዲሁም የተቀናጀ ስትራቴጂና አገር አቀፍ የሆነ የፋይናንስ ትምህርት ፕሮግራም አለመኖር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሞጂዩሉ በሚገባ ተግባራዊ ሲደረግ ወጣቶቹና ጥቃቅን፤ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማቱ የፋይናንስ እውቀታቸውና ግንዛቤያቸው ስለሚያድግ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መሥጠት፣ በራሳቸው መተማመን፣ የተለያዩ የፋይናንስ ገበያ አማራጮችን ማየትና የፋይናንስ ግባቸውን ለማሳካት አቅም እንደሚፈጥርላቸውም አቶ ነቢል ጠቁመዋል፡፡

More News