የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞች የፋይዳ ቁጥር ምዝገባ ትግበራ ይፋ ተደረገ

ለፋይናንስ ሥርዓት አካታችነት፣ ጤናማነትና መረጋጋት ዓይነተኛ ሚና የሚኖረው የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ
በተለይም የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ደንበኞች የፋይዳ ቁጥር ምዝገባ ትግበራ ይፋ ተደረገ።


ሥነሥርዓቱ የተከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በጋራ ባዘጋጁትና ረቡዕ ታህሳስ
17 ቀን 2016 ዓ.ም በሃያት ሬጀንሲ ባካሄዱት መርሐግብር ላይ ነው።


የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ደንበኞችን በብሔራዊ መታወቂያ እንዲመዘገቡ የማድረጉ አስፈላጊነት መሠረታዊ ጉዳይ
የሆነው የተቋማቱ ደንበኞች የፋይዳ ቁጥር ተሠጥቷቸውና የተበዳሪ ደንበኞች መለያ (Unique Identifier) አግኝተው
የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻልነው።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አማካሪ ወይዘሮ ማርታ ኃ/ማርያም በሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ
ንግግር እንደገለጹት፣ ይህ ፕሮጀክት የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት የጠራ የመረጃ አያያዝ እንዲኖራቸውና በቴክኖሎጂ የታገዘ
ዘመናዊ አሠራር እንዲከተሉ ያስችላቸዋል።


በተጨማሪም ተቋማቱ ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲልኩ የሚያግዛቸው
መሆኑንም ወይዘሮ ማርታ ኃ/ማርያም አስረድተዋል።


የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ራሔል አብርሃ በበኩላቸው፣ መርሐግብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ
የሚያስገኘው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ረገድ ሁሉም የፋይናንስ ዘርፉ ተዋናያን በተለይም አነስተኛ
የፋይናንስ ተቋማት ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።


የተቋማቱን ደንበኞች ምዝገባ ለማከናወን የሚችል ተቋም ለማፈላለግ ዓለምአቀፍ ጨረታ ወጥቶ ውድድር የተካሄደ
ሲሆን፣ ውድድሩንም CSM Technologies PVT LTD Joint Venture with Africom Technologies
PLC የተባለ ድርጅት ማሸነፉ ታውቋል።


ድርጅቱ ሥራውን ማከናወን እንዲችል ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት የፋይናንስ ፕሮጀክት ጋር የኮንትራት ስምምነት
የተፈራረመ ሲሆን፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ዘይኑ እና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት የፋይናንስ
ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሮ የመንዝ ወርቅ ግረፍ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።


አሸናፊው ድርጅት የምዝገባ ሥራውን እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 2024 እስከ ጁላይ 2025 ድረስ የሚያካሂድ ሲሆን፣
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማትን ደንበኞች ይመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የድርጅቱን የሥራ ሂደት ተከታትለው ማረጋገጫ ሲሠጡ፣
በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት የፋይናንስ ፕሮጀክት ክፍያውን የሚፈጽም መሆኑ ታውቋል።


በሥነሥርዓቱ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል አቶ ተመልሶ አበበ የክሬዲት ሪፈረንስ እና የሙቫብል ኮላተራል
ሬጂስትሪ ዳይሬክተር፣ አቶ ክፍሌ ነጋሽ የክሬዲት ሬፈረንስ ቢሮ ማኔጀር፣ እንዲሁም ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም
ደግሞ አቶ ሄኖክ ጥላሁን ጉዳዩን አስመልክቶ ጥናቶችን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። አሸናፊው ድርጅትም ስለ
አሠራሩ ገለጻ አቅርቧል።


ሥራው ወደ ትግበራ እንዲሸጋገር የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፣ ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ
ኢንተርፕራይ ልማት ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ሆነው ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል።

More News