05 ነሐሴ 2015 ዓ.ም | አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃና በቀጣይነት ሊቀንሱ የሚችሉ በርካታ የፖሊሲ እርምጃዎች እንዲወሰዱና ወዲያውኑ ሥራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል፡፡
የፖሊሲ እርምጃዎቹ ዳራ
የዋጋ ንረት ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ከባድና የረጅም ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ሕዝቡ ለረጅም ዐመታት በዋጋ ንረት ውስጥ ኖረዋል፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካይ በዓመት 16 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው የዋጋ ንረት ደግሞ ከዚህ አማካይ የዘለለና ከተጠበቀው በላይ የቆየ ክስተት ነው፡፡
ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከማክሮ ኢኮኖሚም ሆነ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ አንጻር ሲታይ ብዙ ጉዳቶች አሉት፡፡ የዋጋ ንረት ቋሚ ገቢ ያላቸው ሰዎችን ትክክለኛ ገቢ ይቀንሳል፤ ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችን ይጎዳል፡፡ በተጨማሪ፣ የዋጋ ንረት በቆየ ቁጥር፣ አሁን በኢትዮጵያ እንደሆነው፣ ሥር የሰደደ ስጋት ይሆናል፡፡ የዋጋ ንረት ይኖራል የሚለው እሳቤ በራሱ ለወደፊቱ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ስለሚያደርግ ሂደቱ በጊዜ ሊገታ ይገባል፡፡
በቅርቡ የታየው የዋጋ ንረት
የዋጋ ንረት ሰኔ 30፣ 2015 መጨረሻ የ29.3 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ30 በመቶ በታች ወርዷል፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ34 በመቶ የዋጋ ንረት ጋር ሲነጻጸር በ5 መቶኛ ነጥብ ቀንሷል፡፡ እንዲሁም በቅርብ ዓመታት በከፍተኛነት ከተመዘገበው የ37 በመቶ የዋጋ ንረት ዝቅ ብሏል፡፡ በዚህ ረገድ መጠነኛ መሻሻል ቢኖርም፣ በቂ እንዳልሆነ ግን ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ምግብ ነክ የዋጋ ንረት አምና ከነበረበት 38 በመቶ ዘንድሮ ወደ 28 በመቶ (በ10 መቶኛ ነጥብ) ዝቅ ያለ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ንረት ግን ከ28 በመቶ ወደ 31 በመቶ (በ3 መቶኛ ነጥብ) አሻቅቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የዋጋ ንረት በግንቦትና በሰኔ ወር መካከል የ3.3 በመቶ ወርሃዊ ጭማሪ ማሳየቱ በኢኮኖሚው ውስጥ የተንሰራፋ የዋጋ ንረት ጫና መኖሩን ያመለክታል፡፡
የዋጋ ንረት መንስኤዎችና የመካከለኛ ጊዜ እይታ
የአቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻ ወጪ መጨመርና ማክሮ ኢኮኖሚአዊ ፖሊሲዎች በተለያየ ደረጃና በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ለዋጋ ንረት መንስኤ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች አካላት ያደረጓቸው የተለየዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 2015 ባደረገው ዝርዝር ግምገማ የአቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻ ወጪ መናር (ውጫዊ ምክንያቶችን ጨምሮ) እና ልል የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች በድምሩ በኢትዮጵያ ለተከሰተው የዋጋ ንረት አስተዋጽኦ እንዳላቸው አመልክቷል፡፡ ለምሳሌ፣ ለዋጋ ንረት አስተዋጽኦ ላላቸው አንዳንድ የአቅርቦት ውስንነትና የማምረቻ ወጪ መናር ምክንያት ከሆኑት መካከል የምግብ ትራንስፖርትና ስርጭትን ሂደት ያስተጓጎሉ የሀገር ውስጥ ግጭቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ የቁልፍ ሸቀጦች (በተለይ የነዳጅ፣ ማዳበሪያና ትራንስፖርት) ወጪ መጨመር ይገኙባቸዋል፡፡ እ.አ.አ. በ2020 አጋማሽ እና በ2022 አጋማሽ መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ 140 ፐርሰንት ፣ የማዳበሪያ ዋጋ በ200 ፐርሰንት፣ የማጓጓዣ ወጪዎች በ300 ፐርሰንት አድገዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ዋጋዎቹ በመጠኑ የረገቡ ቢሆንም፣ የእነዚህ ሸቀጦች የዓለም ዋጋ ጫና በ2014 እና በ2015 በጀት ዓመታት በኢትዮጵያ ለተከሰተው የዋጋ ንረት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
እንዲሁም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተከታታይ በታዩ ውስጣዊና ውጫዊ ክስተቶች፣ ማለትም ኮቪድ፣ ግጭት፣ ድርቅ፣ ዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታዎች ) የተነሣ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች ላላ እንዲሉ መደረጉ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለዋጋ ንረት ብቸኛ ምክንያቶች ባይሆኑም፣ የዋጋ ንረትን የመዋጋት ሥራን እንዳልደገፉ አይዘነጋም፡፡
መጪውን ጊዜ በተመለከተ፣ አሁን ያሉ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች ስንመለከት የዋጋ ንረትን ሊቀንሱ አንዳንዴም ሊያባብሱ የሚችሉ ስጋቶች አሉ፡፡ በአገራችን በብዙ አካባቢዎች ከታየው መልካም የዝናብ ሁኔታ የተነሣ፣ እንዲሁም ከንግድ አጋር አገራት የዋጋ ንረት መውረድና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንዳንድ ሸቀጦች ( ለምሳሌ ማዳበሪያ) ዋጋ መቀነስ ጋር ተያይዞ የምግብ ዋጋ በመጠኑም ቢሆን እንደሚረግብ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ በቅርቡ ከተመዘገበው ወርሃዊ የዋጋ ንረት ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ካሉ የአቅርቦት ተግዳሮቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንዳንድ የሸቀጦች ( ለምሳሌ የነዳጅና የጥራጥሬ እህል) ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ አንጻር ሲገመገም፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳሉ ማየት ይቻላል፡፡ በመሆኑም፣ በመካከለኛው ጊዜ የዋጋ ንረት ስጋት እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃና በቀጣይነት ለመቀነስ ተገቢና ቁጥብ የፖሊሲ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
ለዘላቂ መፍትሔ የቅንጅታዊ አሠራር አስፈላጊነት
ለዋጋ ንረት አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች በርካታ እንደመሆናቸው፣ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የዋጋ ንረት ችግር ለመቅረፍ የሚረዳው መፍትሔ የብዙ ወገኖችንና ዘርፎችን የተቀናጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡
- የአቅርቦት ማሻሻያ እርምጃዎች፡- በሸማቾች የዋጋ ኢንዴክስ የ54 በመቶ ድርሻ ያለውን የምግብ ዋጋ ወሳኝነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቁልፍ ነገር ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ የሚታረሰውን መሬት ስፋት ለመጨመር፣ የውሃ መስኖን ለማስፋፋት፣ የኩታ ገጠም እርሻን ለማበረታታት፣ የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት፣ የቆላማ አካባቢዎችን ግብርና ለማለማመድ፣ በስፋት ለፍጆታ የሚውሉ ሰብሎችን (ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ) ምርት ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ሊቀጥልም ይገባል፡፡ በሌሎች ቁልፍ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ምርት ረገድ ፣ በተለይም ሲሚንቶ፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ትራንስፖርት በመሳሰሉ ዘርፎች ያለውን አቅርቦት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው፡፡
- መዋቅራዊ እርምጃዎች፡- የትራንስፖርት አውታሮችን፣ የሎጂስትክስ ሥርዓትንና የንግድ ሥራ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል የሚረዱ መዋቅራዊ እርምጃዎችን መውሰድ በተለይ በረጅሙ ጊዜ፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን ለማሳለጥና የምርት ገበያን ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ ብሎም ለወደፊቱ የዋጋ ጫናን ለማርገብ ይጠቅማል፡፡
- የፊስካል ፖሊሲ፡- ከላይ ከተጠቀሱት የአቅርቦትና መዋቅራዊ እርምጃዎች በተጨማሪ ፊስካል ፖሊሲም የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠሙ ተከታታይ ጫናዎች ( ኮቪድ፣ ግጭት፣ ድርቅ) የመንግሥት የወጪ ፍላጎት እንዲጨምርና የገቢ ዕድገት እንዲቀንስ በማድረጋቸው የኢትዮጵያ የፊስካል ተግዳሮት ከፍ ብሏል፡፡ የመንግሥት የበጀት ጉድለት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ የውጭ ብድርና እርዳታ ውስን በመሆኑ፣ አብዛኛውን የበጀት ጉድለት ከሀገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች፣ በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚገኝ ብድር፣ መሸፈን ግዴታ ሆኗል፡፡ ለመጪው ዓመት ግን፣ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቅረፍና ማክሮ ኢኮኖሚአዊ መረጋጋትን ለማስፈን ሲባል መርሃዊ አቋም ይዟል፤ የመንግሥት ወጪ ዕድገት በእጅጉ ተገድቧል፤ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አኳያ የበጀት ጉድለት በ2016 በጀት ዓመት እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ ይህም መንግሥት ከሀገር ውስጥ ባንኮች በተለይም ከማዕከላዊ ባንክ የሚኖረውን የፋይናንስ ፍላጎት እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ልዩ ሚና
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን በተመለከተ፣ ባንኩ ፣ በተለይ ከአጭር ጊዜ አኳያ ፣ለዋጋ ንረት መርገብ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድና ሥራ አመራር በያዝነው በጀት ዓመት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ቅድሚያ ሰጥተው በቁርጠኝነት ለመሥራት ተነሣሥተዋል፡፡ ሰፊ ውስጣዊ ግምገማ በማድረግና ያለፈው ዓመት የብድር ዕድገት የዋጋ ንረት የመቀነስ ጥረታችንን ማሰናከሉን በመረዳት በዘንድሮው በጀት ዓመት ለመንግሥትም ሆነ ለግሉ ዘርፍ በሚሰጠው ብድር ዕድገት ላይ ገደብ ለማስቀመጥ ወስነናል፡፡ ከዚህም በመነሣት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ የሚወሰዱ አጠቃላይ እርምጃዎችን እንደሚከተለው አስፍረናል፡-
- እንደ አጠቃላይ ግብ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ ከ20 በመቶ በታች፣ በ2017 ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ይሠራል፡፡
- በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የክሬዲት/የባንክ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ ይገደባል፡፡ በመሆኑም፣ ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋል፡፡
- በያዝነው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር መጠን በእጅጉ በመቀነስ ከአምናው ከሲሶ (ከ1/3ኛ) እንዳይበልጥ፣ በሌላ አነጋገር በ25 ፐርሰንት እንዲገደብ ያደርጋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ቀጥታ ብድርን እንደ የመጨረሻ አማራጭ የሚጠቀመው የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ በበቂ መጠን ለገበያ መቅረብ ሳይችል ሲቀር ብቻ እንደሚሆን መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
- ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
- የወጪ ንግድን በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን ወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ ለማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ ( forex surrender requirement) እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ በአዲሱ መመሪያ መሠረት፣ የሸቀጦችና አገልግሎቶች ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶ ለባንካቸው ያስተላልፉና ቀሪውን 40 በመቶ ወደ ራሳቸው የባንክ ሂሳብ እንዲያስገቡ ተፈቅዷል፡፡
ማጠቃለያ
በዛሬው ዕለት የሚወሰዱ የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች አስፈላጊነትና አግባብነት ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላትና በመላው ህብረተሰባችን ዘንድ ሊታወቅና ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል፡፡ አንደኛ፣ እነዚህ የፖሊሲ እርምጃዎች የባንክ ብድር/ክሬዲት ዕድገትን ይቀንሳሉ እንጂ ብድሩን/ክሬዲቱን አያስቀሩም፡፡ ሁለተኛ፣ የክሬዲት ዕድገትን መግታት በራሱ ግብ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን በቀጣይነት ለመቀነስ የሚደረግ የጋራ ዓላማችን ወሳኝ ክፍል እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሶስተኛ፣ የብድር ጣሪያ እስከ 2016 አጋማሽ ድረስ ብቻ የሚቆይ ጊዜያዊ እርምጃ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ባንኩ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ አገራት ወደሚጠቀሙበት ይበልጥ ዘመናዊ ወደሆነውና፣ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ የሚሸጋገር ይሆናል፡፡ ይህም ሰፊ ዝግጅትና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በዘንድሮውም ሆነ በቀጣዩ በጀት ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዋጋን የማረጋጋት ቁልፍ ኃላፊነቱን በትኩረት ለመወጣትና በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ለረጅም ጊዜ ተጭኖ የቆየውን የዋጋ ንረት በከፍተኛ ደረጃና ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በቁርጠኝነት ይሠራል፡፡