የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትና ግብይትን ይበልጥ የሚያዘምን አሠራር ሊዘረጋ ነው

በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትና ግብይት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ሕብረተሰቡም በተለይም የከተማው ኗሪ ያለጥሬ ገንዘብ እየተገበያየና የአገልግሎት ክፍያዎችን በዲጂታል አግባብ መጠቀምን እየተለማመደ መጥቷል።


የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትና ግብይት የጥሬ ገንዘብን ዝውውር የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ፣ ሕብረተሰቡ ለሥርቆት፣ በእጁ ያለው ገንዘቡም ለእርጅና እንዳይጋለጥ፤ ከባንክ ውጭ የሚዘዋወር የገንዘብ መጠን እንዲቀንስ፣ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ገንዘቡን ለማሳተም የሚወጣ ወጪን እንዳይጨምር ለማድረግ ይረዳል።
የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትና ግብይት ሰዎች ገንዘብን በሚያስፈልጋቸው ጊዜና መጠን እንዲገበያዩበት የሚያስችል፣ ሥራንና ንግድን የሚያቀላጥፍ፣ አጠቃላይ አኗኗርን ቀላል የሚያደርግ መሆኑ ይታመናል። አብዛኛው ኅብረተሰብ በሚገለገልባቸው ቋንቋዎች ሥራ ላይ የዋለ በመሆኑ፣ ሞባይል ስልክ የሚጠቀምና የባንክ ሒሳብ መዝገብ ያለውን ማንኛውም ግለሰብ ተደራሽና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።


የክፍያ አገልግሎትን ከባንኮች በተጨማሪ የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ አውጭዎች (የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሠጭዎች) እና ሌሎች የክፍያ ተቋማት እየተሳተፉበት በመሆኑ፣ ሕብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ለማግኘት እያስቻለው ይገኛል።


በአሁኑ ወቅት 140 ሚሊዮን ዲጂታል አካውንቶች (ሒሳቦች) በባንኮችና ባንክ ባልሆኑ ተቋሟት የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም የዲጂታል ግብይት አገልግሎት እየሰፋና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መሆኑን እንደሚያመለክት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያና ሒሳብ ማወራረጃ ሥርዓት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ዳምጠው ይገልጻሉ። ለአብነት ያህል ባለፈው ዓመት 5 ትሪሊዮን ብር ያህል ገንዘብ በዲጂታል ክፍያ ግብይት መንቀሳቀሱንም ይጠቁማሉ።


ይህንን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን በመላ አገሪቱ ለማስፋፋት እንዲሁም ዘመናዊ፣ ተናባቢና ቀልጣፋ ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከኢትስዊች (Eth-Switch) ጋር በመተባበር ልዩ ልዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከተግባራቱ መካከል አገር አቀፍ የዲጂታል ግብይት ሥርዓትን ለማዘመንና ተናባቢ አሠራርን መዘርጋት ነው።
ባለፈው ሣምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተናባቢ የኪውአር ደረጃ (Standardized INTEROPERABLE QR) አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር አንድ የምክክር መርሐግብር አካሂዷል። ከኢትስዊች (Eth-Switch) ጋር በመተባበር የተካሄደው ይህ መድረክ አገር አቀፍ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማዘመንና ተናባቢ የኪውአር ደረጃ ለመዘርጋት በሚያስችል ሰነድ ላይ ተወያይቷል።


በውይይቱ ወቅት የሰነዱ ዓላማ ምን እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚዎች በሙሉ ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነ፣ ግልጽ፣ ፈጣን፣ ተናባቢ፣ በመላ አገሪቱ የሚተገበር፣ ወጥ የሆነ አሠራር ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን አቶ ሰሎሞን አስረድተዋል።


ይህ ኢትኪውአር ኮድ (EthQR Code) የሚል ሥያሜ የሚኖረው አሠራር ዓለምአቀፍ የአሠራር ልምዶችን መሠረት ያደረገ፣ የክፍያም ሆነ የግብይት ተዋናያንን ሙሉ መረጃ የሚይዝ ነገር ግን ከተወሰኑ አስፈላጊ መረጃዎች በቀር ሌሎቹን በምሥጢር የሚጠብቅ አስተማማኝ ሥርዓት ነው።


ይህ አሠራር ተግባር ላይ ሲውል በርካታ ጠቀሜታዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የዲጂታል ክፍያ አሠራሮችን የተሳለጠ ማድረግ፣ አንዳንድ ስጋቶችን መቆጣጠር፣ የነጋዴዎችንም ሆነ የደንበኞች ግብይት ደህንነቱን ማረጋገጥ ዋነኞቹ ናቸው።


አሠራሩ በአገርአቀፉ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ላይ በተቀመጠውና አስተማማኝ፣ አካታችና ፈጣን የእርስበርስ የክፍያ መሠረተልማቶችን ስለመዘርጋት በሚገልጸው ክፍል መሠረት የሚተገበር መሆኑንም አቶ ሰሎሞን አመልክተዋል።


በውይይቱ ወቅት ከባንኮችና ሌሎች ከክፍያ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከሚሠሩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ በሠጡት ሀሳብ ይህ አዲስ አሠራር ሙሉ በሙሉ ትግበራ ላይ ሲውል አሁን እየታየ ያለውን የዲጂታል መጭበርበር ለመቀነስና የደንበኞች ጥበቃን ለማጠናከር እንደሚረዳ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

More News