ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ አዲስ ፈቃድ ላወጡ አስመጪዎች እና ላኪዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር (NBE Account Number) አሰጣጥን የሚያቀል አዲስ የዲጂታል አገልግሎት አስተዋውቋል።
ይህ አገልግሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥሮች በጉምሩክ ኮሚሽን አንድ መስኮት አገልግሎት (Customs Electronic Single Window – eSW) በኩል ያለምንም ውጣ ውረድ እንዲሰጥ በማስቻል፣ አስተዳደራዊ ሂደቶችን የሚቀንስ እና ፈጣን የንግድ አሰራርን የሚደግፍ ነው።
አዲሱ አገልግሎት የሚመለከተው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ለሚያወጡ እና አዲስ ፈቃድ ላገኙ አስመጪዎች እና ላኪዎች ብቻ ነው። ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ያላቸው የንግድ ተቋማት ለሁሉም የገቢ እና የወጪ ንግድ ግብይቶቻቸው ይጠቀሙበት በነበረው ነባር ቁጥር መጠቀም ይችላሉ።
ይህ አሰራር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገቢ እና የወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ የንግድ አሰራርን ምቹ ለማድረግ፣ እንዲሁም የዲጂታል የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ቀጣይ ጥረት አካል ነው።



