መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስድስተኛ ስብሰባውን መጋቢት 12 ቀን 2018 አካሂዷል፡፡ በተሻሻለው የባንኩ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በየጊዜዉ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ነድፎ ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምከረ-ሐሳቦችን በማቅረብ፣ ያስጸድቃል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት፣የዋጋ ግሽበት፣ የበጀት፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፣ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ እንድምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል፡፡ ኮሚቴው ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት እይታዎች በመነሣት በቦርዱ ፀድቆ ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡
በዚሁ መሠረት፤ ኮሚቴው በውይይቱ ያካተታቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-
- የዋጋ ግሽበት፡- ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመምጣት የካቲት ወር 2018 መጨረሻ ላይ 9.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ከታህሳስ ወር 2018 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የነጠላ አኃዝ ዓላማን ለማሳካት ተችሏል፡፡ በኮሚቴው ግምገማ መሠረት ለዋጋ ግሽበት መቀነስ በተከታታይነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እያደረገ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የበጀት ፖሊሲ ስርዓት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የዋጋ ግሽበትን ከፋፍለን ስናይ፤ ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት የካቲት ወር 2018 መጨረሻ 10.8 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት 14.6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፣ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት 8.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት 15.6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡ የየካቲት ወር 2018 ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት 0.4 በመቶ በመመዝገቡ የዋጋ ንረት በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና እየቀለለ መሄዱን ያመላክታል፡፡ በሌላ መልኩ የዋጋ ግሽበት የወደፊት እይታን በተመለከተ በመካከለኛው ምሥራቅ የተነሱ የጂኦ ፖለቲካዊ ግጭቶች በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረና የአቅርቦት ሰንሰለቶች መቋረጥን እየፈጠረ በመሆኑ ይህ ክስተት በአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ የሥጋቱም ጫና ግጭቱ በሚቆይበት ጊዜ እና መንግሥስት በሚወስዳቸው የመቆጣጠሪያ እርምጃዎች ላይ የሚወሰን ቢሆንም ኮሚቴው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አትኩሮት ሰጥቶበታል፡፡
- ዕድገትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፡- ኮሚቴው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ እና በ2017 በጀት ዓመትም አጠቃላይ ኢኮኖሚው ባለፉት 8 ዓመታት ከተመዘገበዉ የ7.5 በመቶ አማካይ እድገት ከፍ ያለ የ9.2 በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ተገንዝቧል፡፡ ለዚህም የኢኮኖሚ ዕድገት የአገልግሎት ዘርፍ አስተዋጽኦ በነበረበት በ3.1 በመቶ የቆየ ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተዋጽኦ ደግሞ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 2.7 በመቶ ወደ 3.7 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ለዚህም ዋና ምክንያት በማዕድን ዘርፍ የታየው ከፍተኛ እድገት ሲሆን በተለይም የወርቅ ምርት አስተዋጽኦ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 0.1 በመቶ በ10 እጥፍ ዕድገት በማሳየት በ2017 በጀት ዓመት ወደ 1.0 በመቶ ከፍ በማለቱ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ ለዕድገቱ ያለው አስተዋጽኦ ደግሞ ከነበረበት የ2.2 የተወሰነ ጭማሪ በማሳየት በ2017 በጀት ዓመት ወደ 2.3 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች (Composite Indicators of Economic Activities) በ2018 በጀት ዓመት የተጠናከረ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር ያመላከተ ሲሆን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የተመዘገበው አወንታዊ ለውጥ ለእድገቱ አመላካች ሆነዋል፡፡ ለዚህም በኢንዱስትሪው ዘርፍ በሲሚንቶ ምርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ምርት እና በብረታ ብረት ምርት የታዩ መሻሻሎች ከሌሎች አምራች ዘርፎች ጋር ተደምሮ የተነቃቃ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ መኖሩን ያሳያል፡፡ የአገልግለት ዘርፉም እንዲሁ ከፍተኛ አፈጻጸም ያሳየ ሲሆን በተለይም የቱሪስት ፍሰት እና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት /የመንገደኞች እና ዕቃ ማጓጓዝን ጨምሮ/ ከፍተኛ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡ ይሁንናእንደ ቡና፣የቅባት እህሎች የወጪ ሸቀጦች መጠን እንዲሁም የጥሬ ዕቃዎች ገቢ ንግድ ላይ ከባለፈዉ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ታይቷል፡፡
- የገንዘብ ሁኔታ፡- በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) ከአምናው አፈጻጸም ጋር ሲወዳደር ዕድገት ያሳየ ሲሆን መሠረታዊ ገንዘብ (base money) ደግሞ ዕድገቱ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በየካቲት ወር 2018 መጨረሻ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው ጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ39.3 በመቶ፣ መሠረታዊ ገንዘብ (base money) ደግሞ የ43.2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሲያሳዩ፣ ሰኔ ወር 2017 መጨረሻ ከነበረዉ ጋር ሲነጻጸርም በቅደም ተከተል የ22.7 እና የ23.0 በመቶ እድገት አሳይተዋል፡፡ የባንኮች የተከማቸ ብድር ደግሞ 45.3 በመቶ ዓመታዊ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን በየካቲት ወር መጨረሻ ከሰኔ 2017 ጋርም ሲወዳደር የ33.3 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡የባንኮች የብድር አቅርቦት ዕድገት ለጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሌላ መልኩ ለመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገት መጠነኛ ቅናሽ ማሳየት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ ሥርጭት ለመሰብሰብና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማረጋጋት ያደረገው የውጭ ምንዛሪ ግብይት እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡
- የወለድ ተመን ሁኔታ፡- ኮሚቴው የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች የዕድገት ሁኔታ ጥሩ መሆኑን የተነገዘበ ሲሆን ከማስቀመጫ ወለድ ዉጭ ያሉት ተጨባጭ ወለዶች ሁሉ ከዜሮ በላይ ሆነዋል፡፡ የ91-ቀናት የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ የወለድ ምጣኔ ተመን አምና ከነበረበት የ15.2 በመቶ ቅናሽ በማሳየት በየካቲት ወር 2018 መጭረሻ 12.4 በመቶ ሊወርድ ችሏል፡፡ ለዚህም ከባንኮች እና ከሌሎች ድርጅቶች በተጨማሪ ግለሰቦች በገበያው መሳተፋቸው አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን ቆይታ ያለው አማካኝ የወለድ ምጣኔ ተመን በየካቲት ወር መጨረሻ አማካይ ወለዱ 17.9 በመቶ ሆኗል፡፡ በባንኮች መካከል እየተደረገ ያለው የገንዘብ ግብይት ዝውውር ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ የመጣ ሲሆን ከጀመረበት ጥቅምት ወር 2017 መጨረሻ እስከ አሁን ብር 1.97 ትሪሊዮን ደርሷል፡፡
- የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ፡- የባንክ ዘርፉ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ በኮሚቴው የተገመገመ ቢሆንም በአንዳንድ ባንኮች ዘንድ በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ አከል (liquidity) እጥረት መኖሩም ታይቷል፡፡ ይህም በግል ባንኮች ዘንድ በሚታየው ከፍተኛ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ (loan to deposit ratio) ጥምርታ የተንጸባረቀ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁን ላይ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያና (Interbank Money Market) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቋሚ የብድር አገልግሎት (Standing Lending Facility) ለጥሬ ገንዘብ አከል ችግሮች በመፍትሔነት እያገዙ ይገኛሉ፡፡
- የበጀት ሁኔታ፡- ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ ጥንቃቄ የተሞላበት የበጀት ፖሊሲ ስርዓት እንደነበር እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንደነበር ተገንዝቧል፡፡ ይህም በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሰባት ወራት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ ያደረገና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በእጅጉ የሚደግፍ ሆኗል፡፡ ይህም የመሠረታዊ ገንዘብ እድገትን ለመገደብ አስችሏል፡፡ በ2025/26 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሰባት ወራት አጠቃላይ የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ጥመርታ 1.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው 0.7 በመቶ አንጻር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ምንም እንኳ የገቢ አሰባሰብ የ65 በመቶ አመታዊ እድገት ቢያሳይም፣በተመሳሳይ ጊዜ አጠቃላይ ወጪ 48 በመቶ በመጨመሩ ምክንያት አጠቃላይ ጉድለቱ ሊሰፋ ችሏል፡፡ በአንጻሩ የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት በሰባቱ ወራት ብር 136.6 ቢሊዮን በመሰብሰብ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
- የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- በሐምሌ ወር 2016 ከተወሰደው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ኢኮኖሚ ሚዛን (overall balance of payment) ትርፍ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፉ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ እንደሚያመለክት ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስምንት ወራት የኢትዮጵያ የክፍያ ሚዛን ትርፍ አሳይቷል፡፡ በወርቅና በቡና ከፍተኛ እድገት የታየ ሲሆን በግለሰብ ሀዋላ፣ በተጣራ የአገልግሎት ንግድና በካፒታል ሂሳብ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ውጤቶች የውጭ ገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል የተጀመሩ የኢኮኖሚ ልማት ማሻሻያዎች አወንታዊ ተፅእኖ እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማጠናከር እና የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍን ዘላቂነት ለማሻሻል ይረዳል።
- ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እ.ኤ.አ በ2026 እና በ2ዐ27 በቅደም ተከተል 3.3 በመቶ እና 3.2 በመቶ እንደሚሆን የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም (IMF) የጥር ወር 2026 (እ.ኤ.አ) የትንበያ መረጃ ያመላክታል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄዱ ካሉ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ይህ የዕድገት ትንበያ ሊቀንስ እንደሚችል ስጋቶች ይታያሉ፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞም በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የምርት ግብአት ዋጋዎች መጨመር፣ የመግዛት አቅምን ማዳከም እና የፋይናንስ እጥረትን በማስከተል በአጠቃላይ የዓለም አቀፍ ዕድገት እንዲቀንስ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ክስተት በተለይ ነዳጅ አምራች ባልሆኑ አገሮች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር የሚገመት ቢሆንም፣ ተጽእኖው በግጭቱ መጠን፣ ጥልቀት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በሚቆይበት ጊዜ ይወሰናል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ትንተናና ምክረ-ሀሳቦች
ኮሚቴው ከታህሳስ ወር 2018 ጀምሮ የተመዘገበውን የነጠላ አሀዝ የዋጋ ግሽበት በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተወሰደ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ግንዘቤ ወስዷል፡፡ በዚህ ረገድ ባንኩ ያሉትን የፖሊሲ መሳሪያዎች በሙሉ (እንደ አስፈላጊነቱ በተናጠል ወይም በቅንጅት) እንዲጠቀም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ኮሚቴው የነጠላ አሀዝ የዋጋ ግሽበት ዓላማን ለማሳካት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቁርጠኛ አቋም ወስዷል፡፡
በመሆኑም የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) እና ባንኮች የሚሰጡት የተከማቸ ብድር ዓመታዊ የዕድገት መጠን በነበረበት እንዲቀጥል ወስኗል፡፡ ነገር ግን በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችለው ተለዋዋጭ የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ በአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ ከግንዛቤ ለማስገባት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን በንቃት መገምገም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ ተጨማሪ የፖሊሲ እርምጃዎች ያስፈልጉ እንደሆን ለመገምገም በሚያዝያ ወር 2018 መጨረሻ ላይ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ቀደም ብሎ እንዲሰበሰብ ወስኗል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም



