የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማን ቀን ጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ ም አከበሩ።
በባንኩ ቅጥር ግቢ በተካሄደው በዚህ የአከባበር ሥነሥርዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሰንደቅ ዓላማን ተሰቅሏል።
በሥነሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኮርፖሬት ሰርቪስ ክላስተር ም/ገዥ አቶ እዮብ ገ/የሱስ ባደረጉት ንግግር የዘንድሮው በዓል “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን ተናገረው፤ ይህም በተለያዩ ማንነቶችና አስተሳሰቦች ውስጥ ያለን ኢትዮጵያውያን በጋራ የምንጋራትን ውድ ሀገር በመግባባት፣ በመተማመንና በመተባበር ለመጪው ትውልድ የማሻገር ኃላፊነታችንን ያስታውሰናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አቶ እዮብ የሰንደቅ ዓላማ ምንነት ከባንካችን የሥራ ተልዕኮ ጋር የሚያገናኘው ጥልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገራችንን የዋጋ መረጋጋትን የማረጋገጥ፣ የገንዘብና የፋይናንስ ሥርዓት የመጠበቅ፣ የፋይናንስ ተቋማትን ጥንካሬ የማስጠበቅ እንዲሁም ዘመናዊና አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲገነባ የማስቻል ትልቅ ሀገራዊ አደራ የተሸከመ ተቋም መሆኑን በአጽኖት አመልክተዋል።
የገንዘብ ዋጋ መረጋጋት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ፣ የቁጠባ እሴትን ለማስጠበቅ፣ የንግድ ሥራዎች በተሻለ እርግጠኝነት እንዲንቀሳቀሱ ለማገዝና በኢኮኖሚው ውስጥ እምነት እንዲጎለብት በባንኩ ውስጥ የሚሠራ እያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራው ድርሻ ከግል ኃላፊነት በላይ ለሀገር የሚከፈል አስተዋጽኦ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንዲሚገባ አቶ እዮብ አስረድተዋል፡።
“የሰንደቅ ዓላማ ክብር በቃል ብቻ አይገለጽም፤ በተግባር ይረጋገጣል እንጂ” ያሉት ም/ገዥው አክለውም “ለሀገራችን ያለንን ፍቅር በሥራችን ጥራት፣ ለሕዝባችን ያለንን ክብር በምንሰጠው አገልግሎት፣ ለሕግና ለሥነ ምግባር ያለንን ታማኝነት በውሳኔዎቻችን፣ ለአንድነት ያለንን ቁርጠኝነት ደግሞ ከወንድምና እህቶቻችን ጋር በምንሠራው የትብብር ሥራ መገለጥ አለበት” ብለዋል።
አቶ እዮብ ዛሬ በሰንደቃችን ፊት ቆመን ስለ ብሔራዊ መግባባትና ሰለ አንድነት ስናስብ፣ የባንካችንን የሦስት ዓመት ስትራቴጂ በተግባር ለማሳካት በቁርጠኝነት ለመሥራት ቃል በመግባት ይሆናል ብለዋል።
አክለውም “የሙያ ብቃታችንን ለማሳደግ፣ የተቋማችንን አቅም ለማጠናከርና ለሀገራችን ዘላቂ ዕድገት የድርሻችንን ለመወጣት እንደገና ቃል የምንገባበት ነው” ያሉት አቶ እዮብ፣ እያንዳንዳችን የምንሠራው ሥራ ለጋራ ዓላማችን አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘብ፣ በአንድነት፣ በፍጹም ትጋትና ተጠያቂነት የባንካችንን ትልሞች እንድናሳካ አደራ እንዳለብን አስረድተዋል።



