የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዊ ዞን ለተጋላጭ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት መሠረት በመጣል፣ የትምህርት እቃዎችን በማከፋፈል እና በዛፍ ተከላ ኘሮግራም ላይ በመሳተፍ ለማህበረሰቡ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል። እነዚህ ስራዋች የባንኩ ለብሔራዊ ልማት፣ ለአካባቢ ዘላቂነት እና በመላ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ክፍሎችን ለመገንባት የሚሰራውን ስራ የሚያሳይ ቀጣይ ድጋፍ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ማኅበረሰብ ዘንድ ስለተደረገው አቀባበል ከልብ አመስግነዋል።
በየትኛውም አካባቢ የምንኖር ኢትዮጵያውያን እጅግ ተቆራኝተን በአንድነት የምንኖር፣ ሕዝቦች ነን ያሉት የባንኩ ገዥ፣ ይህም አንድነታችን ማንም ሊከፋፍለው የማይችል ልዩ መለያችን ነውና ሁላችንም ጠብቀን ልናቆየው ይገባል ሲሉ ክቡር ገዥ ተናግረዋል።
ዶክተር እዮብ አያይዘውም ”የአዊ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን አስጠብቆ የኖረ፣ የጥንካሬ ምልክት የሆነ ሕዝብ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ ባዘዘው ጫኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር እዮብ ተካልኝና የባንኩ ሠራተኞች በሥፍራው በመገኘታቸው በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረ እንደነበር ለባንኩ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽንና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተናግረዋል።
”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአዲስ አበባ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ፣ በዚያ ላይ ከዋና መንገድ 30 ኪሎ ሜትር ወደ ገጠር ገብቶ ይህን ያህል የወገን አለኝታነቱን ማረጋገጡ በአገው ብሔረሰብም ሆነ በክልሉ ሕዝብ ዘንደ ያለው ከበሬታ የላቀ እንዲሆን አስችሎታል።“ ሲሉ ተናግረዋል።
አካባቢው የሰላምና የልማት ቀጣና ነው ያሉት አቶ ባዘዘው፣ ሕዝቡ እንዲህ ዓይነት ማበረታቻ ማግኘቱ ደግሞ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ይጨምራል፤ ከመንግሥት ጎን ሆኖም ሰላሙን ለመጠበቅ ያስችለዋል ብለዋል ።









